Saturday, March 16, 2013

የኢትዮጵያና የእስራኤል ግንኙነት



             ከቀዳማዊ ምንሊክ እስከ መለስ ዜናዊ
      
ንግሥተ ሳባ
    ሳባ ጀግና ሴት ነበረች፤ ባህሩን አቋርጣ ኢየሩሳሌም ድረስ የተጓዘች ጥበበኛም ነበረች፡፡ የጠቢቡ ሰለሞንን ማስተዋል ያገኘችው ሳባ ባለፀጋና ቸርም ነበረች፡፡
ቁጥር ስፍር የሌለው ወርቅ፣ እጣን፣ ቅመማ ቅመም፣ የዝሆን ጥርስ ገፀ በረከት አቀረበችለት፡፡ ሳባ የፍቅር ሰውም ነበረች፤ ‹‹ሚስቶችህ እንዴት የታደሉ ናቸው›› በማለት የንጉሡን ልብ ቀሰቀሰች፡፡ ሳባ ዲፕሎማትም ነበረች፤ እስራኤልንና ኢትዮጵያን በታሪክ፣ በእምነትና በባህል ያቆራኘውን የመጀመሪያውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መሠረተች፡፡ ሳባ ታሪክ ሠሪም ታሪክ መሥራችም ነበረች፤ ቀዳማዊ ምኒሊክን ወለደች፡፡ ‹‹ማንኛውንም ወራሪ ኃይል የምትመክትልንን›› ታቦተ ጽዮንን አመጣችልን፡፡ ሳባ ታሪክ ናት፣ ልብ ወለድ አይደለችም፡፡ ልብ ወለድ ናት የሚሉት በጊዜ ሒደት ታሪኩ ከፈጠራ ጋር እየተቀላቀለ መለየት እስኪያቅት ድረስ በመደባለቁ ነው፡፡ ስለዚህም ብዙ ጸሐፊዎች ሀቁን ከፈጠራው ለመለየት አስቸጋሪውን ሥራ ከሚሠሩ ይልቅ፣ የሳባና የልጇ የምንሊክ ታሪክ ፈጠራ ነው ማለቱ ይቀላቸዋል፡፡ የስንዴው አዝመራ በአረም ተውጦ አረሙን ከሚያርም ‹‹ዘንድሮ አዝመራ ጠፋ›› ብሎ እንደሚያማርረው ሰነፍ ገበሬ ማለት ነው፡፡ ከሳባና ከልጇ ትክክለኛ ታሪክ ብዙ ልንማርበት እንችላለን፡፡

ከሰሎሞን አርግዛ ተመለሰች፡፡ ሐማሴን ላይም አፈረች፡፡ ማይበላ የምትባለው መንደር (ከአስመራ ከተማ ወጣ ብሎ) ሕፃኑ ምንሊክ ተወለደ፡፡ ትርጓሜው ‹‹ማን ልበልህ፣ ማን ብዬ ልጥራህ?›› እንደማለት ነው፡፡ መልኩ ከአባቱ ከንጉሥ ሰለሞን በልጦ ብታየው፡፡ ከእናቱ ከንግሥት ሳባ በኋላም ነገሠ፡፡ የዚህ ንጉሥ ታሪክም ስንዴና አረሙ እየተደባለቁ ብዙ አይታወቅም፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ምንሊክ (ዘብሔረ ሐማሴን) በኢትዮጵያ የዘመናት ዘውዳዊ ሥርዓት የፈጠረው ተፅዕኖ በአገሪቱ ታሪክ ከተነሱት ነገሥታት ሁሉ የጐላ ነው፡፡ በተለይም በሃያኛው ክፍለ ዘመን የተነሱትና የመጨረሻው ‹‹ሰለሞናዊ ንጉሥ›› የነበሩት አፄ ኃይለ ሥላሴ የነገሱበት ዘመን ዘመናዊትዋ እስራኤል ከነችግሮችዋ የተመሠረተችበት ጊዜ ስለነበር፣ በዚህ በቀዳማዊ ምኒሊክ ዘር ሐረግ ምክንያት ብዙ ውስብስብ ችግሮች ተከስተዋል፡፡ ኢትዮጵያና እስራኤል በፖለቲካው (በውጭ ግንኙነት) ረገድ ሳባ ከመሠረተችው ግንኙነት የሚነሳ ቢሆንም፣ በሁለቱም ሕዝቦች መካከል የዘለቀው ታሪካዊ ግንኙነት ግን ከዚያም በላይ የሰፋ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ (ብሉይ ኪዳን) ከዓለም ቋንቋዎች ሁሉ ቀድሞ ከእብራይስጥ ቋንቋ የተረጐመው ወደ ግዕዝ ነው፡፡ ይህ የአጋጣሚ ጉዳይ ሊሆን አይችልም፡፡ ይልቁንም ‹‹የዓባይን መነሻ ለማየት›› በአሥራ ስምንተኛው ክፍለ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ የተጓዘው ስኮትላንዳዊው ጄምስ ብሩስ ‹‹በግዕዝና በእብራይስጥ መካከል ያለው መመሳሰል የአጋጣሚ ጉዳይ ነው ለማለት ይከብደኛል፤›› ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡አከራካሪው ነገር ሳባ ኢትዮጵያዊ ንግሥት ነበረች ወይስ የመናዊት? የሚለው ነው፡፡ ምክንያቱም በየመን ውስጥ ሸባ የሚባል አገር ስላለና የመኖችም ሳባ (አዜብ፣ ማክዳ) የእኛ ናት ብለው ስለሚከራከሩ ነው፡፡ አንድ አገር በነበሩበት ጊዜ የተነሳች ንግሥት ሳትሆን አትቀርም፡፡ ግዛትዋ እስከ የመን (ሸባ) ድረስ ሰፊ ስለነበረም የሳባ ንግሥት ተባለች፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ባሉ ምዕራፎች አይሁዳዊ መሠረት አለኝ ብሎ የሚያምነው የአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘውዳዊ መንግሥት በሞአ አንበሳ ዘእምነገድ ይሁዳ ዓርማው ምክንያት ምን ያህል ጣጣ ውስጥ እንደገባ፣ ችግሩ በተለየ መልኩ ወደ ደርግ ዘመንም እንዴት እንደተሻገረና ከኢሕአዴግ መምጣት በኋላ አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ እንዴት እንደተጀመረ ለክቡራን አንባቢዎች እናቀርባለን፡፡ 

እስራኤልና አፄ ኃይለ ሥላሴ
    ለ333 ዓመታት የዘለቀው የዛጉዌ (አገው) ሥርወ መንግስት በሰላማዊ ሽግግር ሥልጣኑን ለሰሎሞናዊው ሐረግ አስረከበ (በ1270 ዓም)።ሐረጉ እየተቆረጠም እየተቀጠለም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ድረስ ደረሰ፡፡ ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ (የይሁዳው ዘር አንበሳ አሸነፈ) የሚለውን ዓርማ መለያቸው ሆነ፡፡ ይህ በአገር ውስጥ በተለይም በተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ዘንድ አንድነትና መተማመንን የመፍጠር ኃይል የነበረው ቢሆንም፣ በአጠቃላዩ የአገሪቱ ፖለቲካ ጥንካሬና የውጭ ግንኙነት ረገድ ግን ብዙ መዘዞችን አስከትሏል፡፡ በውስጥ ይህን የኢትዮጵያን መንግሥት ‹‹አይሁዳዊነት›› ወይም የአንድ እምነት አድሎአዊነት የሙስሊሞችን መብት የሚጋፋ ሲሆን፣ በውጭ ደግሞ ከእስራኤል ይልቅ በኢትዮጵያ ህልውናና ደኅንነት ላይ ተፅዕኖ ማሳደር የሚችሉ ጐረቤት አገሮችን ጥርጣሬ ላይ የሚጥል ነበር፡፡ በሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ምክንያትም የአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት በውጭም በውስጥም ግጭት ውስጥ እየገባ፣ ውጥረቱንም ለማላላት ሲል ከእስራኤል ጋር እንደማንኛውም (Normal) አገር ሊመሠርተው ይገባ የነበረውን ትስስር ‹‹እየተሸማቀቀ›› በጓዳ ግንኙነት ተወስኖ እንዲቀር አድርጎታል፡፡ በአንድ በኩል በአፍሪካ አንድነትና ነፃነት፣ በፀረ ቅኝ ግዛት ትግል አርዓያነታቸው በሌላ በኩል በዓረቦችና በሙስሊሞች እንደ ወራሪ ኃይል ከምትታየው አገር ጐን መቆማቸው፣ ንጉሠ ነገሥቱን በሁለት እግር ሁለት ዛፍ የመውጣት ያህል አስቸጋሪ አጣብቂኝ ውስጥ እንዲገቡ አስገድዷቸዋል፡፡ 

ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍጻሜ ማግስት የተቆረቆረችው ዘመናዊት እስራኤልና ፍልስጥኤም በሁለት መንግሥታት መፍትሔ (Two State Solution) መርህ መሠረት፣ መሬት ለማከለከል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድምፅ በሰጠበት ወቅት ኢትዮጵያ የዓረብ ወዳጆቿን ‹‹ላለማስቀየም›› ስትል የእስራኤልን በፍልስጥኤም ምድር መመሥረት በድምፅ ተአቅቦ አለፈችው (.. 1947)፡፡ ግብፅና ሶሪያ ግንባር ፈጥረው እስራኤል በኃይል የያዘቻቸውን ግዛቶች በኃይል ለማስመለስ በከፈቱት ጦርነት ወቅት ኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ሊከታት ይችል የነበረ ውጥረት ውስጥ ገባች፡፡ ይኸውም ዓረቦችን (የሙስሊም ኃይሎችን) የመደገፍ ወይም ሞአ አንበሳውን (እስራኤልን) የመደገፍ ፖሊሲና የፖለቲካ ጥቅም ተጋጩ፡፡ በዚህ ጊዜ የዓረብ መንግሥታት በኢትዮጵያ ላይ ኃይለኛ ጫና አሳረፉ፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ዋና ጽሕፈት ቤት በአስቸኳይ ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ካይሮ እንዲዛወር ሊቢያና ቱኒዝያ አመለከቱ፡፡ በአገር ውስጥም የሃይማኖት ግጭት እንዲነሳና ዓረቦችና እስራኤሎች በተዋጉ ስለጦርነቱ መነሾ ምንም ያልሰማውም ሁሉ ድንጋይ ሊወራወር ሆነ፡፡ ‹‹የዓረቦች ይውጡ›› ቅስቀሳም ተጀመረ፡፡ ለሰላም ሲባል የተሻለው አማራጭ እስራኤልን ማውገዝና ለግብፅና ለሶሪያ ድጋፍ መስጠት ነበር፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴም ይህን ለማድረግ ተገደዱ፡፡ ይህ ከዘውዳዊው ሥርዓት መውደቅ አንድ ዓመት ቀደም ሲል የታየው ታሪካዊ ክስተት በንጉሡ በኩል የሚከተሉት በጐ ጐኖች ታሳቢ ተደርገው የተወሰደ አቋም ሳይሆን አይቀርም፡፡
1.    ኢትዮጵያን በዓረቡና በሙስሊም መንግሥታት ዘንድ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ       ማዕቀብ እንዳይገጥማት፣
2.    የነዳጅ ማዕቀብ እንዳይጣልባት፣
3.    የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ጽሕፈት ቤት ከአዲስ አበባ እንዲነሳ በፊትም ቢሆን ችግር ይፈጥሩ የነበሩት አገሮች በቂ ምክንያት ሊያገኙ ይችሉ ስለነበር፣ 
4.    ለኦጋዴንና ለኤርትራ ተዋጊዎች ይሰጥ የነበረው ወታደራዊ ዕርዳታ ይቆማል ወይም ጋብ ሊል ይችላል ከሚል ግምት፣
5.    በአገር ውስጥ መታየት የጀመረው ከፋፋይ እንቅስቀሴ ወደማያስፈልግ ሃይማኖታዊ ቀውስ እንዳይሄድ ለመቆጣጠር ነበር፡፡ 

የኢትዮጵያ መንግሥት (... 1973) የእስራኤልን መንግሥት በማውገዙ በትክክል ብዙዎቹ ታሳቢዎች የተሳኩ ሲሆን፣ ለኤርትራና ለሶማሊያ ተዋጊዎች ይደረግ የነበረው ድጋፍ ግን ሊቆም አልቻለም፡፡ በሌላ በኩል በተወሰደው አቋም ምክንያት ኢትዮጵያ ከዘላቂ ዕድገትዋ አንፃር በጣም ካደገችው አገር (እስራኤል) በዘመናዊ እርሻ፣ ትምህርትና ወታደራዊ ቴክኖሎጂ ረገድ ልታገኝ ይገባት የነበረውን ዕርዳታና ድጋፍ አጥታለች፡፡ ግብፆችን በመደገፍ ኢትዮጵያ እስራኤልን የሸሸችው ይደርስባት በነበረው ውግዘትና ዛቻ ተገዳ ቢሆንም፣ በጊዜ ሒደት ግን ብዙዎቹ የዓረብ መንግሥታት ከእስራኤል ጋር ተራ በተራ የእርቅና የሰላም ውል ፈርመዋል፡፡ 

ሌላው ንጉሡ የዓረብ ጦርነትን በመደገፍ እስራኤሎችን ከኢትዮጵያ ማስወጣታቸው 66 ንቅናቄ በኋላ የተከሰተው ሁኔታ ነው፡፡ በሁለቱ የንዋይ ወንድማማቾች የተጀመረውን 1953 መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በማክሸፍ በኩል እስራኤል (ከአሜሪካ ጋር) ትልቅ ሚና ተጫውታለች፡፡ ይኸውም አፄ ኃይለ ሥላሴ ለጉብኝት ከሄዱበት አገር (ብራዚል) ሆነው መፈንቅለ መንግሥቱን እንዲያከሽፉ ትዕዛዝ እንዲሰጡ ከምድር ጦር አዛዦች ጋር በቴሌግራም መልዕክት እንዲገናኙ ማድረጓ ነው፡፡ በዚህ ግንኙነት ምክንያት የኢትዮጵያ የምድር ጦር በመፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎቹ ላይ የማያወላውል ዕርምጃ እንዲወሰድ ትልቅ ብርታት ሰጥቶታል፡፡ ቅልበሳውንም በሙሉ ልብ እንዲያከናውነው የወኔና የሞራል ስንቅ አግኝቷል፡፡ በተጨማሪም 53 መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሌላ ሁለት ተሞክረው የተዳፈኑ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዎች በማክሸፍ በኩል በንጉሡ ጊዜ የነበሩት እስራኤላውያን የደኅንነት አማካሪዎች ትልቅ ሥራ እንደሠሩ ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ አንድ የእስራኤል ወታደራዊ መኰንን ጽፈዋል፡፡

የስድስቱ ቀናት ጦርነት እየተባለ በሚታወቀው .. 1973 ጦርነት አፄ ኃይለ ሥላሴ የእስራኤልን ኤምባሲ በመዝጋት የእስራኤልን ወታደራዊና የደኅንነት አማካሪዎችን ጭምር እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጥተዋል፡፡ ይህ የአፍሪካንና የዓረብ ኅብረቶች አቋሞችን ያከበረ ውሳኔ ግን የንጉሠ ነገሥቱንና የቤተሰቦቻቸውን ሕይወትና ደኅንነት ዋጋ ሳያስከፍል አልቀረም፡፡ ከዚህ ቀደም አንድ የሚታወቅ (የእነ መንግሥቱ ነዋይ) ሌሎች ደግሞ ሁለት ተዳፍነው የቀሩ ሙከራዎችን በማክሸፍና የንጉሠ ነገሥቱን ደኅንነት በመጠበቅ በኩል ሞሳድ (የእስራኤል የስለላ ድርጅት) ሚና መጫወቱን ተመልክተናል፡፡ 66 ሕዝባዊ ንቅናቄ ወቅት ግን እስራኤል ኤምባሲዋን ዘግታ በመውጣቷ ሕዝባዊ ማዕበሉን እንኳን መቀልበሱ ባትችል፣ አፄ ኃይለ ሥላሴንና ቤተሰቦቻቸውን ከአገር ማስወጣት ትችል እንደነበር (ከደርግ ጋር በመደራደር ወይም በብልኃት) መገመት አያስቸግርም፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነትዋን በጣም በከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባት ሲያማክሩና ከእስራኤል ጋር የሚኖረው ግንኙነትም በቀዘቀዘ (Low Profile) መንገድ መካሄድ እንደሚገባው ያሳስቡ ከነበሩት ባለሥልጣናት ግንባር ቀደሙ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር (በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር) አክሊሉ ሀብተ ወልድ ነበሩ፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ የኤርትራ ገዥ የነበሩት ልዑል አሥራት ካሣ (የፖለቲካና የደኅንነት አማካሪዎቻቸው የሞሳድ ሰዎች ነበሩ) በአፍቃሪ እስራኤልነት የሚታወቁ ናቸው፡፡ ያም ሆኖ ግን ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ እስራኤል ከኢትዮጵያ ጋር በጊዜው በነበራት የጋራ የፀጥታና የደኅንነት ጉዳይ ምክንያት ግልጽና ደረጃውን የጠበቀ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመገንባት ፅኑ ፍላጐት የነበራት ቢሆንም፣ የሙስሊም ዜጎችዋን ዝንባሌ በማየት፣ የአፍሪካ ተምሳሌትነትዋን ከግምት በማስገባትና ከባለፀጋዎቹ ዓረብ መንግሥታት ሊመጣባት የሚችለውን ጣጣ በመፍራት፣ በርካታ አገራዊ ጥቅሞችዋን ትታ የእስራኤል የመጥፊያዋ ሰዓት በተቃረበበት በዚያ ቀውጢ ሰዓት ለዓረቦች ቆማለች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እነፕሬዚዳንት ገማል አብደል ናስር ኢትዮጵያ ከእስራኤል ጋር የነበራትን የተቀዛቀዘ ግንኙነት በማጋነንና በማራገብ ከዕለት ወደዕለት ከጐረቤቶችዋ ጋር በጠላትነት እንድትተያይ ብዙ ጥረዋል፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ... 1957 ከአንድ የእንግሊዝ ጋዜጠኛ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ‹‹ኮሎኔል ናስር ሙስሊሞች ዜጐቻችንን በማነሳሳት አገራችንን ሊያበጣብጥ እየጣረ ነው፤›› ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸው ነበር፡፡ 

የኤርትራ መገንጠልና የቀይ ባህር ሁኔታ
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውሳኔ ኤርትራ ‹‹በፌዴሬሽን›› ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል ተወሰነ፡፡ ፌዴሬሽኑ ኤርትራ በውስጥ ጉዳይዋ በአነስተኛ ጉዳዮች ካልሆነ በአብዛኛው በዘውዳዊው ሥርዓት ሥር ያስገባት ውሳኔ ነበር፡፡ ስለዚህም ፌዴሬሽኑ አጨቃጫቂ ለነበረው የሕዝበ ውሳኔ ድምፅ አሰጣጥ ሒደት እልባት ለመስጠት የተደረገ የግብር ይውጣ መደምደሚያ እንጂ፣ ለኤርትራ ፖለቲካዊ ችግር መሠረታዊ መፍትሔ የሚሰጥ ቁልፍ አለነበረም ብንል ይሻላል፡፡ ስለሆነም የፌዴሬሽኑ ጥምረት ብዙም ሳይቆይ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ትዕዛዝ ፈረሰና ኤርትራ አሥራ አራተኛዋ ጠቅላይ ግዛት ሆነች፡፡ (ከዛሬ 55 ዓመት በፊት) ኃያላኑ መንግሥታት ግን ይህን የተባበሩት መንግሥታት ውሳኔ ጥሰት አልተቃወሙም፤ አልተገረሙም፡፡ ድርጊቱን በዝምታ እንዲቀበሉት ያበቋቸው የሚከተሉትን በጊዜው የነበሩ ሁኔታዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ 

1.    በቀይ ባህር አካባቢ (በግብፅ መሪነት) እየተጠናከረ በመሄድ ላይ የነበረውን ዓረባዊነት ለመቋቋም ኢትዮጵያ እንደሁነኛ አጋር በመውሰዷ፣ 
2.    በሶቭየት ኅብረት ድጋፍ በአፍሪካ ነፃ በወጡ አገሮች ውስጥ እየተስፋፋ የመጣውን ኮሙኒስታዊ ሥርዓት ለማዳከም የኢትዮጵያ ድጋፍ በጣም አስፈላጊ ስለነበር፣
3.    በኤርትራ ውስጥ ቅኝ ግዛት የወለደው ካፒታሊስታዊ ሥርዓት የኢትዮጵያን የፊውዳል ሥርዓት ሊያናጋ እንደሚችል ስጋት በመፈጠሩ አፄ ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያ አንድነትና ህልውና ምሰሶ ተደርገው በመታመናቸው፣
4.    በግብፅ ድጋፍ በኤርትራ ቆላማ አካባቢዎች የተጀመሩት እስላማዊ እንቅስቃሴዎች የምዕራባውያንንም ሆነ የዘውዳዊውን ሥርዓት አደጋ ላይ እንደሚጥል በመታሰቡ፣5.    የኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ሙሉ በሙሉ መዋሀድ የንጉሠ ነገሥቱን መንግሥት በኢኮኖሚና በፖለቲካ የሚያጠናክር በመሆኑ ምዕራባውያንም ኢትዮጵያ ከመፈራረስ የምትድነው ዘውዱ ሲጠናከር ነው የሚል አመለካከት ስለነበራቸው፣

ንጉሠ ነገሥቱንም በማናቸውም መንገድ መደገፍ ለቀጣናው ሰላምና ደኅንነት ወሳኝ ነገር ነው የሚል አቋም ስለተያዘ፣ ኃይለ ሥላሴን በማጠናከርና የኤርትራን ትግል በግልጽ በመቃወም በኩል እስራኤል ግንባር ቀደምዋ አገር ነበረች፡፡ምዕራባውያን ከስትራቴጂያዊ ጥቅማቸው አኳያ መዝነው መጀመሪያ ኤርትራ በፌዴሬሽን እንድትጣመር፣ ከዚያም ሙሉ በሙሉ እንድትዋሀድ ቢፈቅዱም ያስከተለው ጦስ ግን ዘርዝረን የምንጨርሰው አይደለም፡፡ ከፌዴሬሽኑም ጊዜ በፊት በስደት ይኖሩ የነበሩት የኤርትራ ወጣት ሙስሊሞች እንዲሁም በፌዴሬሽኑ መፍረስ የተቆጩት ክርስቲያኖች በገማል አብደል ናስር አስተባባሪነት ከአሌክሳንድሪያ ከተማ ወጣ ብሎ በተዘጋጀላቸው ወታደራዊ ማሠልጠኛ ሠፈር 1958 .. ለትጥቅ ትግል ሥልጠና ገቡ፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላም በመስከረም ወር ወደ ኤርትራ በረሃ ዘልቀው የትጥቅ ትግል ጀመሩ፡፡ በመጨረሻም በሙስሊም ኃይሎች መሪነት ተጠናክሮ የወጣው በአጭሩ ጀብሃ እየተባለ የሚጠራው ድርጅት ነበር፡፡ ኢሳያስ አፈወርቂም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢንጂነሪንግ ትምህርታቸውን አቋርጠው ከጀብሃ ጋር ተቀላቀሉ፡፡ ጀብሃ በደገኛው ሕዝብ ላይ የሚፈጽመውን መድልዎ በመቃወምና ጀብሃን ጥለው በመውጣት ከሰባት ጓዶቻቸው ጋር በአጭሩ ሻዕቢያ የተባለውን ግንባር መሠረቱ፡፡ ሙስሊሙንና ክርስቲያኑን ኤርትራዊ በማስተባበር ለድል ለማብቃት ቻሉ፡፡ በኤርትራ ፖለቲካ ሁለቱንም ሃይማኖቶች አስማምቶ መምራት የሚችል ማንኛውም ኃይል ብዙ ነገር መሥራት ይችላል፡፡ 
የሚገርመው ነገር የኤርትራ ትግል ‹‹ዓረባዊና እስላማዊ›› ተደርጐ ሲገመት የነበረ ቢሆንም አቶ ኢሳያስ የኤርትራ ፕሬዚዳንት ከሆኑ በኋላ ከዓረቦች ይልቅ ቀስ በቀስ ወዳጅ ያደረጉት እስራአልን ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር የመሠረቱት ግንኙነት በአብዛኛው በኢትዮጵያና በኤርትራ ሕዝቦች መካከል ካለው ቤተሰባዊነት እንዲሁም ሁለቱም መሪ ድርጅቶች በትግል ጊዜ ከነበራቸው የጋራ መስዋዕትነት ታሪክ የሚመነጭ ቢሆንም፣ ከእስራኤል ጋር የመሠረቱት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ግን ለየት ያለ ትኩረትን የሚስብ ነው፡፡ እስራኤል የኤርትራውያንን ትግል ለማዳከም የአፄ ኃይለ ሥላሴንም ሆነ የፕሬዚዳንት መንግሥቱን መንግሥታት በሚስጥርም ቢሆን በወታደራዊ አቅም ስትደግፍ ነው የቆየችው፡፡ ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኋላም ቢሆን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ከዓረብ መንግሥታት ጋር ያላቸው ግንኙነት በዕርዳታ ላይ የተመሠረተ እንጂ ስትራቴጂያዊ ግብ ያለው አይመስልም፡፡ (ለዚህም ነው አንዴ ሲስማሙ ሌላ ጊዜ ሲጣሉ የሚታዩት) የእስራኤልንና የኢትዮጵያን ወታደራዊ መደጋገፍ ለመቋቋምና ነፃነት ለመቀዳጀት የግድ ወደ ዓረብ መንግሥታት ሠፈር መግባት የነበረበት ሻዕቢያ ከነፃነት በኋላ ግን ነፃነቱን ያለማወላወል የተቀበለችውን እስራኤል ሥጋት ላይ በሚጥል መልኩ ቀይ ባህርን ‹‹ዓረባዊ›› ለማድረግ የወሰደው ግዙፍ ዕርምጃ የለም፡፡ 
በእርግጥ ኤርትራን ቀስፎ የያዛትን የኢኮኖሚ ችግር ለመቋቋም ሲባል የሚደረጉ ነገሮች አሉ (በተለይም ወግ አጥባቂ ባለነዳጅ ዓረብ መንግሥታትን ለማስደሰት)፡፡ ቢሆንም ግን አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ የእስራኤልን ደኅንነት ሥጋት ላይ በሚጥል ሁኔታ የኤርትራን የቀይ ባህር ክልል ለአክራሪ ኃይሎች አሳልፈው የማሰጡበት ምክንያት የለም፡፡ አቶ ኢሳያስ ከእስራኤሎች ጋር መወዳጀት እንጂ መጋጨት የማይችሉበትን ታሪካዊ ምክንያት እርሳቸው ራሳቸው ያውቁታል፡፡ ሐረትስ የተባለው የእስራኤል ጋዜጣ ... ዲሴምበር 12 ቀን 2012 እንደዘገበው፣ አቶ ኢሳያስ የዳህላክን ደሴቶች ለእስራኤል ወታደራዊ ተግባር እንዳከራዩት ሁሉ የአሰብ ወደብንም ለኢራን አከራይተዋል፡፡ ነገር ግን ከኢራን ጋር የሚኖረው ግንኙነት በነዳጅ ጥቅም ላይ የተመሠረተ እንጂ መሠረታዊና በሩቅ ግብ ላይ ያነጣጠረ አይደለም፡፡ ከእስራኤል ጋር ያላቸው ግንኙነት ግን በጋራ የደኅንነትና የህልውና ጥያቄ ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡

ሻዕቢያ ኤርትራን ነፃ ካወጣ በኋላ አቶ ኢሳይያስ ወዲያውኑ ከወሰዷቸው ዕርምጃዎች አንዱ ከኢትዮጵያ ጋር ጠንካራ ግንኙነትን መፍጠር ነው፡፡ ይህ ያልተመደ ነው፡፡ ለሰላሳ ዓመታት እርስ በርስ በጦርነት ተላልቀው ከሰላም በኋላ አገሮች በቀላሉ ወደ እርቅና ሰላም አይመጡም፡፡ የኤርትራና የኢትዮጵያ ሁኔታ ግን ከእርቅና ከሰላም በላይ ነው፡፡ አቶ ኢሳያስ የአያት ቅድመ አያቶቻቸው አገር የሆነውን ትግራይን በሁለት አጃቢዎች ብቻ እየተጠበቁ ነበር በላንድክሩዘር በየሳምንቱ የሚመላለሱበት፡፡ የአዲስ አበባ ጉዞአቸውም ያን ያህል ያስደስታቸው ነበር፡፡ ይህ ለሁለቱ አገሮች ቀጣይ ግንኙነትም ሆነ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ቁልፍ የሚባል ዕርምጃ ነበር፡፡ እንዲያውም በሪፈረንደሙ ጊዜ ከድምፅ አሰጣጡ በኋላ ድፍን ኤርትራዊ የሰጠው ቃል ‹‹ተስፋችንና ምኞታችን አሁንም ከኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር አብሮ መኖር ነው፤›› የሚል ነበር፡፡ በወቅቱ አንድ ታዛቢ እንደተናገሩት ሪፈረንደሙ የጦርነት ይቁም ሕዝበ ውሳኔ እንጂ የመገንጠልና የመለያየት ዓላማን ያዘለ አይመስልም ነበር፡፡ አቶ ኢሳያስ ይህን የኤርትራውያንን ተስፋና ምኞት (የኢትዮጵያውያንም ተስፋና ምኞት) በሚገልጽ መልኩ ‹‹ኤርትራና ኢትዮጵያ በፌዴሬሽን ወይም በኮንፌዴሬሽን እንደገና የሚተሳሰሩበትን ጊዜ እንጠብቃለን፤›› በማለት ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለቀረበላቸው ቃለ መጠይቅ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ከኤርትራ መገንጠል በኋላ ቀይ ባህር ‹‹የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች መፈንጫ ይሆናል›› የሚለው የበርካታ ኢትዮጵያውያን ሥጋት ሊገፈው ችሏል፡፡ ነገር ግን ይህ በጐ ጅምር ብዙ ሳይቆይ በሚያሳዝን መልኩ ተቀለበሰ፡፡ ‹‹በኢትዮጵያ ብር እየተገበያየንና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ደንቦችና መመርያዎች እየተመራን ነፃ አገር ነን ለማለት አንችልም፡፡ ኢትዮጵያ በአሰብ ወደብ እየተጠቀመች ኤርትራ የቀይ ባህር ባለቤት ሆናለች ብለን አፍ ሞልተን መናገር አንችልም፤›› የሚሉ ኃይሎች (በተለይም ምሁራን) በኤርትራ ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ተጠናከሩ፡፡ አቶ ኢሳያስም፣ ‹‹አሰብ ኢትዮጵያ ካልተጠቀመችበት የግመል ውኃ መጠጪያ ከመሆን አያልፍም፤›› ሲሉ ምላሽ ሰጡ፡፡ የገንዘቡ ጥያቄ ግን እንደዚህ የሚታለፍ ነገር አልሆነም፡፡ እውነት ነው፤ ነፃ አገር ማለት የራሷ ገንዘብ ያላት አገር ማለት ነው፡፡ ነገር ግን እንዴትና መቼ የማለው (በተለይም በኢኮኖሚ በኩል በኢትዮጵያ ላይ ሙሉ በመሉ ጥገኛ የሆነችው ኤርትራ) ጥያቄ በደንብ መጠናት ይገባው ነበር፡፡ 
ኢኮኖሚክስን ከፖለቲካ ጋር ካላስተሳሰሩ አደጋው የከፋ ሊሆን ይችላል፡፡ በኤርትራውያን ምሁራና በሻዕቢያ አመራሮች በኩል ግን ይህ የታሰበ አይመስልም፡፡ ኤርትራ የራሷን ገንዘብ ሳታትም በኢትዮጵያ በኩል የሚኖረው ምላሽ ምን ሊሆን ይችላል? መቼ ተግባራዊ ቢሆንስ ይመረጣል? በብር እየተገበያየን ብንቆይስ ከኢትዮጵያና ከኤርትራ ልዩ ታሪካዊ/ሕዝባዊ ግንኙነት አኳያ ጉዳቱ ምንድን ነው? ወዘተ፤ የሻዕቢያ መንግሥት ለእነዚህ ጥያቄዎች ጊዜና ትዕግስት አልነበረውም፡፡ ምሁራኑ ያቀረቧቸው ጥናታዊ ጽሑፎች ከሁለቱም አገሮች ተጨባጭ ሁኔታዎች፣ በተለይም ከኤርትራ የተሰባበረ ኢኮኖሚ አንፃር ተጨባጭነትና መፍትሔ ሰጭነት የጐደላቸው ቢሆኑም፣ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተግባራዊ አደረጉት፡፡ 
ኢሕአዴግ ከሻዕቢያ ጋር ከበረሃ ትግል አንስቶ ጥንቃቄና ትዕግስት የተሞላበት ግንኙነት በመመሥረት ቀጣናው የአክራሪዎችና የፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች መፈንጫ እንዳይሆኑ ትልቅ ሥራ ሠርቷል፡፡ ከኤርትራ መገንጠል በኋላም ይኸው የትዕግስትና የችሎ ማለፍ አቋሙን ቀጥሎበታል፡፡ ይህ ሻዕቢያን ከመፍራት ወይም ከኢትዮጵያ ጥቅም ይልቅ ለኤርትራ መቆምን ሳይሆን የሚያሳየው በሻዕቢያ ወረራ ምክንያት የደረሰው ዓይነት እልቂትና ውድመት እንዳይከሰት ጥንቃቄ ከማድረግ የመነጨ ነው፡፡ ይህም የሻዕቢያ አመራርና ፖሊሲ እውነተኛ ባህርይና ተፈጥሮ በትክክል ከመገንዘብ የተነሳ ነው፡፡ የሻዕቢያ ባሥልጣናት መገመት ሲገባቸው ነገር ግን ባልጠበቁት ሁኔታ የኢሕአዴግ መንግሥት የቀድሞውን ብር በአዲስ ገንዘብ ቀይሮ አሳትሞ ለሥርጭት ማዘጋጀቱ ተገለጸ፡፡ ይሁንና ይህ በራሱ ችግር አላስከተለም ነበር፡፡ አንድ ናቅፋና አንድ ብር እኩል የምንዛሪ ዋጋ እንዲኖራቸው ስምምነት ተደርሶ ነበርና፡፡

 
ነገር ግን በሁለቱም አገሮች መካከል የሚኖረው የንግድ ልውውጥ እንደማንኛውም የዓለም ክፍል በውጭ ምንዛሪ ሊሆን ይገባል የሚለውን የኢሕአዴግ መንግሥት አቋም ሻዕቢያ አምርሮ ተቃወመው፡፡ በድንበር አካባቢ ለሚደረጉ ባህላዊ ግብይቶች (እስከ ናቅፋ/ብር/2000) ድረስ ግን የውጭ ምንዛሪ ሳያስፈልግ ማለት ነው፡፡ ሻዕቢያ ሐሳቡ የተለመደ ዓለም አቀፋዊ አሠራርና ሕግ መሆኑን ዘንግቶት ‹‹ወያኔ ኤርትራን ለመጨፍለቅ ያቀደው ዕቅድ ነው›› በማለት ሐሳቡን በፅኑ ኮነነው፡፡ የኢትዮጵያ ግዛት የሆነችው ባድመ እንደ ሰበብ ቀረበች፡፡ ‹‹አንቺው ታመጪው አንቺው ታሮጪው›› እንዲሉ በሰላምና በፍቅር መኖር የጀመሩትን ወንድማማች ሕዝቦች እንደገና ያጨፋጭፍ ገባ፡፡ መጨረሻውም የሻዕቢያ እብጠት መተንፈስና ፕሬዚዳንት ኢሳያስም ከዓለም ተገልለው በብቸኝነት መኖር ሆኗል፡፡ ስንት ደም የፈሰሰበትና ስንትና ስንት የተነገረለት ቀይ ባህርም እውነትም የግመሎች ውኃ መጠጫ ሆኖ ቀረ፡፡ በትግሉ ጊዜ እንደ ተራማጅ፣ አብዮታዊና ተአምረኛ ታጋይ ሲታዩ የነበሩት ኢሳያስ አፈወርቂ አሁን በብስለታቸው ጊዜ ጦረኛ፣ አፍራሽ፣ አድኃሪና ብቸኛ መሪ ሆነዋል፡፡  

ቀይ ባህርና የግብፅና የእስራኤል ስምምነት
ደርግ የኤርትራን የመገንጠል ጥያቄ ከቀይ ባህር ጋር ብቻ በማስተሳሰር በዓረብ ሊግ አባል አገሮች ላይ የዛቻና የማጥላላት ዘመቻ በሰፊው ማካሄዱ በአገር ውስጥ ሰፊ ድጋፍን አስገኝቶለት ነበር፡፡ ትግሉን ‹‹የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች›› (ዓረቦች) ያቀነባበሩት ሸር እንጂ በኢትዮጵያ ገዢዎች ያልተስተካከለ ፖሊሲ ምክንያት የተፈጠረ ችግር እንዳልሆነ ተደርጎ ሲካሄድ የነበረው የፕሮፓጋንዳ ሥራ ጦርነቱን እንዲመርና እንዲራዘም ከማድረጉም በላይ፣ ደርግን እንደ አገር አለኝታ ሆኖ በማይገባው ሥልጣን ላይ እንዲቆይ አስችሎታል፡፡ በሌላ በኩል ግን ‹‹የዓረብ ቡችሎች›› ፕሮፓጋንዳው ምክንያት የኤርትራ የመገንጠል ትግል በአንድ ወይም በሁለት የዓረብ መንግሥታት ብቻ መደገፉ ቀርቶ የመላውን የሙስሊምና የዓረብ ዓለም ትኩረት ይስብ ጀመር፡፡ በተለይ ቢያንስ ሃምሳ በመቶው ሕዝቧ የእስልምና አማኝ የሆነው ኤርትራ ጦርነቱ የሃይማኖት ጦርነት ተደርጎ በደርግ መንግሥት የፕሮፓጋንዳ ማሽነሪ በተደጋጋሚ በመለፈፉ፣ የኤርትራ ነፃ አውጪ ግንባሮች ከጥቂት ዓረብ መንግሥታት አልፈው የመላው ሙስሊምና ዓረብ መንግሥታት ድጋፍና ዕርዳታ እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡ 
ከፍልስጥኤም ነፃ አውጪ ግንባር ሳይቀር ወታደራዊ ድጋፍ ሲያገኝ የነበረው የኤርትራ ንቅናቄ ገና ከመጀመሪያው እስራኤል አልደገፈችውም፣ ተቃውማዋለች፡፡ ለምን ቢባል ለደኅንነትዋና ለብሔራዊ ጥቅሟ ሲባል፡፡ በግልባጩ ሲነበብ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ በኋላ በዓረቦች ላይ የከረረና የመረረ የጥላቻ አቋም የያዘው የደርግ መንግሥት የጦርነት ሥልቱም ሆነ የፕሮፓጋንዳ ማሽነሪው በጠላት ላይ ጠላት እያበዛ በታሪክ የኢትዮጵያ ወዳጆች የነበሩት እነኢራንና እነሳዑዲ ዓረቢያ ሳይቀሩ የኤርትራውያኖቹን ትግል መደገፍ ጀመሩ፡፡ እስራኤል የጠላቶቼ ወዳጅ ጠላቴ ነው በሚል አቋም የመገንጠሉን ጥያቄ ለማዳከም ከአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ጋር እንደቆመችው ሁሉ ደርግንም በተመጠነ መልኩ ትደግፍ ነበር፡፡ ዋናው ነገር ሲጀመር የሙስሊም ወንድማማቾች መልክና ተፅዕኖ ይዞ የተነሳው የኤርትራ ትግል ምናልባት በአፍሪካ ዓረብ ኃይሎች የበላይነት ቢጠናቀቅ የእስራኤልን ደኅንነትና ብሔራዊ ጥቅም የሚጎዳ ነው ተብሎ በመታመኑ ነበር፡፡ 
ይሁንና ጦርነቱ በተጋጋለበት ነገር ግን ፕሬዚዳንት መንግሥቱ የእስራኤል የጦር አማካሪዎችን በሙሉ ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ባዘዙበት በዚያ ቀውጢ ሰዓት በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ አንድ ልዩ ታሪካዊ ድርጊት ተፈጸመ፡፡ ይኸውም ሁለቱ ደመኛ ጠላት መንግሥታት የእስራኤልና የግብፅ መሪዎች በሰላም አብሮ ለመኖር በአሜሪካ አደራዳሪነት የፈረሙት የሰላም ቃል ኪዳን ነው፡፡ ይህ አብዛኛው የዓረብና የሙስሊም ሕዝቦችን (ግብፃውያንን ጭምር) ያበሳጨውና የፍልስጥኤሞችን ተስፋ ያጨለመው ለዓመታት በምስጢር ድርድር ሲካሄድበት ቆይቶ ካምፕ ዴቪድ ላይ የተፈረመው የሰላም ውል ሌላ ራሱን የቻለ ትልቅ ጂኦ ፖለቲካዊ ውጤት አስከተለ፡፡ ይኸውም የቀይ ባህርም ሆነ የኤርትራ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ መክሰም፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ በእስራኤል (እንዲሁም በአሜሪካ) ያገኙት የነበረው ትኩረት መቀዝቀዝና በአፍሪካም ሆነ በተቀረው ዓለም ደርግ ያቀርባቸው የነበሩት የብሔራዊ ደኅንነትና ህልውና ስጋቶች ተቀባይነት ማጣት ናቸው፡፡ የኢትዮ እስራኤል ልዩ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ማብቂያ ጊዜ መቃረቡንም አመላካች ክስተት ነበር፡፡ ከካምፕ ዴቪድ የሰላም ስምምነት በኋላ እስራኤል ከዓረቡ ዓለም ጋር የነበራትን የጦርትና የእርስ በርስ መጠፋፋት ፖሊሲ እያቀዘቀዘች በሄደች ቁጥር የቀይ ባህር አካባቢም የቀውስና ያለመረጋጋት ቀጣና መሆኑ ቀርቶ የንግድ፣ የትብብርና የሰላም ባህር መሆን ጀመረ፡፡ ደርግ ግን የተከሰተውን አዲስ የቀጣናውን አሠላለፍ ተጠቅሞ ፖሊሲውን እንደማስተካከል አሁንም ባረጀውና ባፈጀው ‹‹ዓረቦች በጀብሃ ሻዕቢያ አማካይነት የኢትዮጵያን አንገት ሊቆርጡ ተነስተውብናል›› በማለት ዓለም አቀፍ ዘመቻውን ቀጠለ፡፡ ከሰላም ውሉ በኋላ ግን ራሷን የዓረቦች መሪ አድርጋ በምታልመው ግብፅና በጥንታዊቷ የኢትዮጵያ አጋር እስራኤል መካከል ዘላቂ ሰላም በመውረዱ ቅስቀሳውና አቤቱታው በዓለም ፊት ተዓማኒነት ሊያገኝ አልቻለም፡፡ 
ከግብፅና እስራኤል መስማማት በኋላም እስራኤል ኢትዮጵያን በወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅም ‹‹በአፍሪካ ምድር ግብፅን የምትገዳደር አገር›› ለማድረግ ይዛው የነበረውን ዕቅድ አቋረጠች፡፡ በሌላ በኩል ከላይ እንደተመለከትነው ኤርትራን ማስገንጠል ቀይ ባህርን ለዓረቦች አሳልፎ በመስጠት ኢትዮጵያን በጠላቶች የተከበበች አገር ማድረግ ነው የሚለው ሥጋት እንዲሁ ሕዝቡን ለማያቋርጥ ጦርነት ከሚያነሳሳ በቀር፣ ቢያንስ በእስራኤል አመለካከት ተጨባጭ ጂኦ ፖለቲካዊ ችግር መሆኑ አብቅቶለታል፡፡ ከዚያ ጊዜ ወዲህ (.. 1979 በእኛ ዘመን አቆጣጠር 1971 .) የኤርትራ (ቀይ ባህር) መገንጠል ኢትዮጵያን የራሷ የሆነ የባህር ወደብ እንዳይኖራት ከሚያደርጋት ውጪ፣ አካባቢው ለኢትዮጵያ (ለእስራኤል) የደኅንነትና የህልውና ሥጋት ምንጭ ሊሆን አይችልም የሚለው መደምደሚያ በእስራኤል መንግሥት እንደ አቋም ተይዟል፡፡ ከዚያ ጊዜ ወዲህ እስራኤል በኢትዮጵያ ላይ የቀረ ትኩረት ነበራት ቢባል ለብዙ ዓመታት ሳይነሳ የኖረው የቤተ እስራኤላውያን (ፈላሾች) እንቆቅልሽ ነበር፡፡ ስለዚህም እስራኤል እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ በጣም ዝቅ ባለ ደረጃም ቢሆን ከፕሬዚዳንት መንግሥቱ ጋር ሚስጥራዊ ግንኙነቷን አላቋረጠችም፡፡ 

የቤተ እስራኤላውያን ጉዞ
እስራኤል የፈላሻዎቹን ጉዳይ እንደ አጀንዳ ለንጉሠ ነገሥቱ አቅርባ አታውቅም፡፡ በራሷ በኩል ዝግጅት ባለማድረጓ አንድ ምክንያት ሊሆን ቢችልም፣ ወትሮም ቢሆን በሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ዓርማቸው የዓረቦችና የአፍሪካውያን ፊት ሲገርፋቸው የኖሩት አፄ ኃይለ ሥላሴ የጥቁር አይሁዶቹ (ፈላሾቹ) ጉዳይ ቢቀሰቀስ ችግሩን የሚያባብስ ሆኖ በመገኘቱ ነበር፡፡ ደርግ ወደ ሥልጣን መጥቶ በኢትዮጵያ ውስጥ ሥር ሰዶ ከኖረው ረሃብና ድርቅ በተጨማሪ የእርስ በርስ ጦርነትና የስደት ማዕበል አገሪቱን ማመስ ሲጀምር የቤተ እስራኤላውያኑ ጉዳይ ፈጥጦ መውጣት ጀመረ፡፡ .. 1977 የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተመረጡት ሚንሃይም ቤጊን አጀንዳውን ከምር አቀረቡት፡፡ አይሁዳውያኑ በአጣዳፊ ሁኔታ ከኢትዮጵያ ስለሚወጡበት መንገድም ዕቅድ መንደፍ ተጀመረ፡፡ ለጥድፊያው የሚከተሉትን ሁኔታዎች እንደምክንያት ማቅረብ ይቻላል፡፡ 

1.    ከካምፕ ዴቪድ ስምምነት መጀመር አንስቶ እስራኤል በኢትዮጵያ ላይ የነበራት ፍላጎት እየቀነሰ በመሄዱ፣ ምናልባት ግንኙነቱ ቢቋረጥ የቤተ እስራኤላውያኑን ጉዞ ቶሎ ማጠናቀቅ ግዴታ በመሆኑ፤
2.    እስራኤል በኢትዮጵያ ምትክ ግብፅን እንደ ስትራቴጃዊ አጋር ማየት በመጀመር በፈላሻዎቹ አጀንዳ ምክንያት በኢትዮጵያ ላይ ሊደርስ የሚችለው (በዓረቦች በኩል) አሉታዊ ተፅዕኖ ጥቅምን እንደማይጎዳ እስራኤል በመገንዘብዋ፤ 
3.    ደርግ እንደ ወዳጅ መንግሥት ቢያዝም ከግጭትና ከጦርነት ውጪ የአፄ ኃይለ ሥላሴን መንግሥት ያህል ተፅዕኖ የመፍጠር አጋርነት የራቀው መንግሥት ሆኖ በመገኘቱ፤
4.    አገሪቱን በተለይም ቤተ እስራኤላውያኑ ይኖሩበት የነበረው ሰሜናዊ ኢትዮጵያ በከፋ ድርቅ፣ ረሃብ፣ ስደትና ጦርነት ይበለብ ስነበር ጉዞውን በአፋጣኝ መጀመሩ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተመናመነ የሄደውን ቤተ እስራኤላውያን ከእልቂት ለማዳን አማራጭ ያልነበረው ግዴታ ስለነበር፤ 
5.    ፕሬዚዳንት መንግሥቱ መጀመሪያ አካባቢ ቤተ እስራኤላውያኑ እንዲጓዙ ለመፍቀድ የእስራኤል የጦር መሣሪያ አቅርቦትን እንደ ቅድመ ሁኔታ አቅርበው የነበረ ሲሆን፣ በኋላ ላይ ግን .. 1978 የእስራኤል የጦር አማካሪዎችን ከኢትዮጵያ አስወጥተዋል (የግንኙነቱ ሚስጥራዊነት በእስራኤል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሞሼ ዳያን ይፋ በመውጣቱና በመክሸፉ) ፡፡

መንግሥቱ ‹‹ኮሙኒስት›› እየሆኑ ወደ ሶቭየቶች እየተጠጉ ሲሄዱ በእስራኤሎች በኩል ሥጋት ተፈጠረ፡፡ ይኸውም ፈላሾቹን ቶሎ ለማስወጣት ዘዴ ማፈላለግ ተጀመረ፡፡ ለመንግሥት ከሶቭየቶች የጦር መሣርያ በገፍ መጉረፍ ሲጀምር ቤተ እስራኤላውያኑ እንዲሄዱ ለመፍቀድ ለድርድር የሚቀመጡበትን በር ጠረቀሙ፡፡ መንግሥቱ ግን እንደወትሮው ልባቸው ከእስራኤል አልተለየም፡፡ የእስራኤሎች ወታደራዊ ንቃት፣ ብቃት፣ ቅልጥፍናና ለመስዋዕት ዝግጁነት በተለይም የአየር ወላዶቻቸውና የኮማንዶዎቻቸው ብቃት፣ እንዲሁም የጦር መሣሪያዎቻቸው ጥራትና ጥንካሬ ገና ሐረር 3 ክፍለ ጦር እያሉ ያውቁታልና፡፡ በእስራኤሎች እግር ሶቭየቶችና ኩባዎች እንዲሁም የምሥራቅ ጀርመን የስለላ ባለሙያዎች ቢተኩም፣ እስራኤሎች ዜጎቻቸውን ስለሚያጓጉዙበት አፋጣኝ መንገድ በፕሬዚዳንት መንግሥቱ ላይ ግፊት ማድረግን አላቆሙም፡፡ በተለይም 1977 .. ድርቅ የሰሜን ኢትዮጵያን ምድር ሰው አልባ ባደረገው ጊዜ እስራኤል ዜጎችዋን ለማዳን ለዘመቻ ተንቀሳቀሰች፡፡ ዘመቻው በሁለት ዋና ምዕራፎች የተከፈለ ሲሆን፣ በድርቁ ጊዜ የተከናወነው ‹‹ዘመቻ ሙሴ›› (Operation Moses) እየተባለ የሚጠራው ነው፡፡ ሁለተኛውና አዲስ አበባ በኢሕአዴግ ሠራዊት የመድፍ ርቀት ተከባ በነበረበት ሰዓታት ውስጥ የተፈጸመውና ‹‹ዘመቻ ሰሎሞን›› (Operation Solomon) የሚባለው ነው፡፡ በዘመቻ ሙሴ አማካይነት በሰባ ሰባቱ ድርቅ ጊዜ አንድ ላይ ተሰባስበው ሱዳን የተሻገሩት ቤተ እስራኤላውያን በተቀናጀና ሚስጥራዊነቱ በተጠበቀ አኳኋን ካረፉባቸው መጠለያ ሠፈሮች ለአንድ ዓመት በተካሄዱ የአውሮፕላን በረራዎች ጉዞው በጥንቃቄ ተደርጎ 7,000 ቤተ እስራኤላውያን የተጓጓዙበት ዘመቻ ነው፡፡ ጉዞው ከሱዳን ተነስቶ የግብፅን የአየር ክልል በማቋረጥ ወደ አውሮፓ ከዚያም ወደ ቴል አቪቭ የተደረገ ነው፡፡ በዚህ ዘመቻ እስራኤል ራሷ፣ አሜሪካ (በገንዘብ ድጋፍና ግብፅን በማግባባት) እንዲሁም ምናልባት ሱዳን (እንዳላወቀች በዝምታ ጉዞውን በመፍቀድ) ተባብረዋል፡፡ በረራው በሌሊት የሚደረግ ከጥንስሱ አንስቶ በከፍተኛ ሚስጥር የተያዘ ቢሆንም፣ በመጨረሻ ግን በፈረንሳይ ጋዜጦች አማካይነት በመናፈሱ 4,000 ያህል ስደተኛ ቤተ እስራኤላውያን በሱዳን መጠለያ ሠፈሮች እንደተጣበቡ ለመቆየት ተገደዱ፡፡ 
የኢሕአዴግና የሻዕቢያ ኃይሎች እየገፉ መምጣት፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ማዝገም፣ የፕሬዚዳንት ሚካኤል ጎርባቼቭ የተሃድሶ ፕሮግራምና የጦር መሣሪያ ዕርዳታ መቋረጥ የደርግ ኢሠፓን ሥርዓት ከሥሩ ይነቀንቀው ጀመር፡፡ የእስራኤል የጦር መሣሪያ፣ የስለላና የእርሻ ቴክኖሎጂ ድጋፎች ደርጉን ለማቆየት አስፈላጊ የዕድሜ ማራዘሚያ ኪኒኖች ነበሩ፡፡ እስራኤል በበኩልዋ በኤምባሲዋ ዙሪያ ተኮልኩለው የሠፈሩትን ፈላሻዎች በአፋጣኝና በአስተማማኝ መንገድ ልታሻግራቸው  የምትችለው እስከዚያ ጊዜ ድረስ መንምኖ ሆኖም ሳይበጠስ የቆየውን የውስጥ ለውስጥ ግንኙነት ከማጠንከር ሌላ አማራጭ አልነበራትም፡፡ ደርግ ከመውደቂያው ሁለት ዓመታት ቀደም ብሎ አቅሙ፣ ጉልበቱና መንፈሱ ሙሉ ለሙሉ ተሸርሽሮ ባለቀበት ሰዓት የቆፍጣናዎቹን የእስራኤል የጦር ጀኔራሎች ሙሉ ድጋፍ ማግኘት ወሳኝ ጉዳይ ነበር፡፡ በሶቭየት ድጋፍና ዕርዳታ በመተማመን ችላ ብሎት የተወውን የፈላሾች ጥያቄ እንደ እስራኤሎቹ ሁሉ ጊዜው ደርሶ ለአፋጣኝ ዕርምጃ ለውይይት ክፍት አደረገ፡፡ ሕዝባዊ አመኔታና ድጋፍ ስላልነበረው፣ በፓርቲውና በጦር ጀኔራሎች መካከል በአንድ በኩል፣ በጀኔራሎቹና ተገዶ በዘመተው ሠራዊት መካከል በሌላ በኩል መግባባት በመጥፋቱ ምክንያት፣ ጦርነቱን ማሸነፍ ያቃተውን የደርግ መንግሥት የውጊያ ፍላጎት ያለቀበትን ሠራዊት መንፈስ ለመጠገን የሚያስችለው ዘመናዊ የጦር መሣሪያ በጠየቀው መጠን ባይሆንም ቀርቦለታል፡፡ ዕርዳታው ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን የጦርነቱን መልክ ቀየረው፡፡ ቢሆንም የፍፃሜውን አቅጣጫ ሊቀይር አልቻለም፡፡ ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር በጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ቆሞ ይጠባበቅ ነበር፡፡ 
የኢሕአዴግ ሠራዊት አዲስ አበባን በመድፍ ርቀት አጥሮ ያለምንም ደም መፍሰስ ዘልቆ የሚገባበትን ሁኔታ ያመቻች ጀመር፡፡ የፍፃሜው መጨረሻ ደረሰ፡፡ እስራኤሎች ዜጎቻቸውን ለማስወጣት በፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አጎት በካሣ ከበደ ተደራዳሪነት ውሉን ፈጸሙ፡፡ ፕሬዚዳንቱ ፈላሻዎቹን ለመልቀቅ የጠየቁትን ያህል ቦምብና ጥፋት ባለማግኘታቸው ቅሬታ ተሰምቷቸው ድርድሩ አሜሪካኖቹም ጣልቃ እየገቡበት ለስድስት ወራት ያለማቋረጥ ተካሂዷል፡፡ ፍፃሜው ሲደርስ እስራኤልና ፕሬዚዳንቱ የጦር መሣሪያ አቅርቦቱ በገንዘብ እንዲሆን ተስማሙ (የጦር መሣሪያ ቢከማች ከእንግዲህ ምን ሊደረግ!)፡፡ ተደራዳሪው የመንግሥቱ አጎት በፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽ የቀድሞው የአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ሩዲ ሮሽዊትዝ አማካይነት የተለቀቀውን 35 ሚሊዮን ዶላር ለፕሬዚዳንቱ እንዲያስረክቡ ተሳካላቸው፡፡ በሃያ አራት ሰዓታት የአውሮፕላን በረራዎች 15,000 ቤተ እስራኤላውያን ወደ እስራኤል ተጓዙ፡፡ ይህም ዘመቻ ሰሎሞን (Operation Solomon) ተብሎ የሚታወቀው ነው፡፡

እስራኤልና የኢሕአዴግ መንግሥት 
ኢሕአዴግ ወደ መሀል አገር ሲገባ ኤምባሲዎቻቸውን ሳይዘጉ ከተቀበሉት በጣም ጥቂት አገሮች አንዷ እስራኤል ናት፡፡ ኢሕአዴግ አዲስ አበባን እንደተቆጣጠረ እዚህ በቀሩት ቤተ እስራኤላውያንና በሌሎች ዓበይት ጉዳዮች ዙሪያ እስራኤሎች ጎልማሳውን የኢሕአዴግ መሪ መለስ ዜናዊን ከጥቂት ቀናት በፊት የገቡበት ቤተ መንግሥታት ውስጥ አነጋገሯቸው፡፡ በመጀመሪያ ያስደነቃቸው የአዲሱ መሪ አቀራረብ ነበር፡፡ ንቀታቸውን ሲየዩ በአሥራ ሰባት ዓመታት ውጣ ውረድና ድካም የመጡ አይመስሉም፡፡ ትህትናቸው አንድ ባለድል ሠራዊት መርተው የመጡ በጭራሽ አይመስሉም፡፡ ግልጽነታቸውና የመጣውን ሐሳብ በሐሳብ የመሞገት ዝግጁነታቸው ከጥናትና ከምርምር እንጂ ከጦር አውድማ የተመለሱ በፍፁም አይመስሉም፡፡ ለቤተ እስራኤላውያኑ ጉዳይ ለመለስ ያልተጠበቀ ሐሳብ አቀረቡላቸው፡፡ ቤተ እስራኤላውያኑ በቅድሚያ ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ልዩነቱ የእምነት ነው፡፡ ስለዚህ እኛ አንድ ኢሕአዴግ የፈላሻዎቹን ጉዞ የምናየው ከሌላ ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ መብት በተለየ ዓይን አይደለም፡፡ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ከአገሩ መውጣትና መግባት የዜግነት ክብሩና መብቱ የሆነውን ያህል፣ ፈላሾችም እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ቪዛ እስካገኙ ድረስ በማንኛውም ጊዜ ከአገር የመውጣትና ወደ አገራቸው የመመለስ ሙሉ መብት አላቸው፡፡ 
እኛ እንደ ኢሕአዴግ ነጥቡን የምንመለከተው ከዚህ አንፃር ነው በማለት አብራሩላቸው፡፡ ይህን ፈረንጆቹ ‹‹Paradigm Shift›› ይሉታል፡፡ ‹‹የአመለካከት ለውጥ›› የሚለው ቃል እንኳን ሙሉ ለሙሉ አይገልጸውም፡፡ በፈላሾች ላይ ለዘመናት ሲደርስ የኖረው መድልዎና መገለል፣ እንዲሁም ሲፈጠር የነበረውን ድብብቆሽና አለመግባባት የሚያስወግድ አዲስ አስተሳሰብ ነው፡፡ ፈላሻዎችን እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ አይቶ እንዲወጡ ብቻ ሳይሆን፣ እንዲወጡም እንዲገቡም ጭምር የዜግነት መብታቸውን ማጎናፀፍ ለችግሩ በጣም የቀለለ መፍትሔ የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ፣ በሌሊት በጨለማ እየተጓጓዝን ግብፅ ምን አለ? ሶሪያስ ምን አለ? ወዘተ ሳይባል በግልጽ በብርሃን ዜጎቿን ለማጓጓዝ የሚያስችል መሠረታዊ የአስተሳሰብ ለውጥ ነው፡፡ 

የኢሕአዴግ መንግሥት የቤተ እስራኤላውያን ፖሊሲ በዚህ መስመር የተቃኘ ነው፡፡ መውጣትና መግባት የዜግነት መብት ስለሆነ የተለየ ዘመቻ ወይም ኦፕሬሽን አያስፈልግም፡፡ ከዚያ ጊዜ ወዲህም ፈላሾች መውጫቸውና መግቢያቸው የዘመቻ ግርግር የሌለበት ፀጥተኛ ጉዞ ሊሆን ችሏል፡፡ ይህ የአስተሳሰብ ለውጥ በሁለቱ አገሮች መካከል ሊኖር የሚገባውን ትክክለኛ አቅጣጫ እንዲይዝ አስችሏል፡፡ በድብብቆሽና በጦር መሣሪያ አቅርቦት ድርድር ተገድቦ የቆው የቤተ እስራኤላውያን ወገኖቻችን ከአገር የመውጣትና የመግባት መብት ከመረጋገጡም በላይ፣ በእነሱ ጉዳይ ምክንያት በተለያዩ የዓረብ አገሮች መገናኛ ብዙኃን ሲራገብ የኖረውንም የኢትዮጵያን ስም የማጥፋት ዘመቻ እንዲቆም አድርጎታል፡፡ ዋናውና ጎጂው የአገራችን ስም የተነሳበት ጉዳይ በተለይ ደርግ ወገኖቹን በሚጨርስበት ቦምብና ጥይት ለውጥ ዜጎቹን በመሸጥ የሰው ኃይል እያጠረው በመሄድ ላይ ያለውን የእስራኤል መከላከያ ኃይል ለማጠናከር ዜጎቹን እየሸጠ ነው የሚል ነበር፡፡ ይህ የኢትዮጵያን ገጽታ በእጅጉ የጎዳው ነገር አሁን ቆሟል፣ ሊያነሳ የሚችልም የለም፡፡ 
በተጨማሪም አስተሳሰቡና በአስተሳሰቡ ላይ ተመሥርቶ የተቀየሰው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ኢትዮጵያ የምትሻውን ጥቅም ከአስራኤል እንድታገኝ የጋረዳትን ‹‹ዓይነ ጥላ›› የገፈፈ ነው፡፡ ‹‹Israel is after all a normal state›› ቀደም ሲል ከመለኮታዊ ጉዳዮች ጋር እየተያያዘ፣ ከገንጣይ አስገንጣይ ፖለቲካ ጋር እየተቆራኘ፣ ኢትዮጵያ በልበ ሙሉነት ከእስራኤልም ሆነ ከዓረብ ወንድሞቻችን ጋር ሩቅ ያለመ ስትራቴጂያዊ ግንኙነት እንዳትመሠርት የነበረው አመለካከት ትልቅ ጋሬጣ ሆኖ ቆይቷል፡፡ 
አሁን የተያዘው አቅጣጫ ፈላሾችን እንደ ማንኛውም ዜጋ፣ ከእስራኤል ጋርም እንደ ማንኛውም አገር በጋራ መብትና ጥቅም ላይ የተመሠረተ ግንኙነትን የሚፈጥር በመሆኑ፣ በቀጥታ በዚህ ምክንያት ከጎረቤቶቻችንም ሆነ ከሌሎች የዓረብና ሙስሊም መንግሥታት ጋር የነበረውን የእርስ በርስ መጠራጠርና መሳሳብ የሚያስቀር ነው፡፡ በተጨማሪም የኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን መምጣቱን ተከትሎ የሚከተሉት ለውጦች (ዕድገቶች) ተከስተዋል፡፡
·       የኤርትራ ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ መፈታቱም በኢትዮጵያ (በእስራኤል) እና በዓረቡ ዓለም መካከል የውጥረት አጀንዳ መሆን ማብቃቱ፣
·       ቀይ ባህር የውጥረት ቀጣና መሆን ማክተሙ፣
·       በኢሕአዴግ የተመሠረተው መንግሥት ከማንኛውም ሃይማኖት ነፃና ገለልተኛ መሆኑ፣ ከእስራኤል ጋር የተመሠረተው አዲስ ግንኙነትም አገሪቱን እንደ ማንኛውም አገር በጋራ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ላይ ብቻ ያተኮረ ግንኙነት እንዲሆን ማስቻሉ፣
·       ‹‹ከመለኮታዊነት›› እና ‹‹ከሚስጥራዊነት›› የተለየ በይፋ በሚታወቅ የጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ አዲስ የግንኙነት ምዕራፍ መከፈቱ፣
·       ከዓረብ አገሮች ጋር የተመሠረተው አዲስ ግንኙነት ከእስራኤል ጋር ከተመሠረተው ግንኙነት በባህሪዩ አንድ ወጥ፣ ከሁሉም ጋር በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተና በተጨባጭ መስፈርት ላይ የተመሠረተ መሆን መቻሉ፣
·       የናይል ወንዝ ለተፋሰሱ አገሮች የጋራ ጥቅም መዋል እንደሚኖርበት ቢያንስ በመርህ ደረጃ በሁሉም አገሮች ግንዛቤና ተቀባይነት ማግኘት መጀመሩ፣
·       የአገሪቱ ሕዝባዊ አንድነትና ውስጣዊ መረጋጋት እየተሻሸለ መሄዱ፣
ከፍ ሲል የጠቀስናቸውና ሌሎች የታዩ መሻሻሎች የኢትዮጵያን የውጭ ተጋላጭነት (Vulnerability) እየቀረፉ፣ በራስ የመተማመንና በተጨባጭ መስፈርቶች ላይ የተመሠረቱ የውጭ ግንኙነቶች ፖሊሲዎችን በማምጣትመልካም ሁኔታዎችንአምጥተዋል፡፡

መደምደሚያ 
ዛሬ ብዙ ነገሮች ተለውጠዋል፡፡ የግብፅና የእስራኤል ውጥረት ተወግዷል፡፡ ቀይ ባህር የኢትዮጵያ የሥጋት ምንጭ መሆኑ አክትሟል፡፡ ከሃይማኖት አድልዎና ተፅዕኖ ነፃ የሆነ መንግሥት ቆሟል፡፡ ኤርትራም ብትሆን ከነፃነት አንስቶ ከእስራኤል ጋር መልካም ግንኙነት መሥርታለች፡፡ ዋናውና ትልቁ ነገር ከኢትዮጵያም ከኤርትራም በላይ በርካታ የዓረብ አገሮች ከእስራኤል ጋር የተጠናከረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን መሥርተዋል፡፡ በፍልስጥኤም ሕዝብ መብት አለመከበር ምክንያት የመካከለኛው ምሥራቅ ውጥረት አሁንም ያልተወገደ ቢሆንም፣ ከግብፅና ከእስራኤል ስምምነት በኋላ ግን ብዙ ለውጦች ተከስተዋል፡፡
 
ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገትዋና ውስጣዊ መረጋጋትዋ እየጎለበተ በሄደ ቁጥር ከማንኛውም አገር ጋር የሚኖራት ግንኙነት በግልጽ በሚታወቁና ተሰፍረው በሚለኩ መመዘኛዎች መሠረት እንደሚሆን የታወቀ ነው፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴም ሆነ በደርግ መንግሥት ጊዜ ኢትዮጵያ ይገጥማት የነበረው ችግር በአብዛኛው ከውስጥ ድክመቶችዋ የሚመነጩ ነበሩ፡፡ የሞአ አንበሳው ጣጣ፣ የድህነቱና የእርስ በርስ ጦርነቱ፣ ወዘተ ችግሮች ከእስራኤል ጋርም ሆነ ከዓረቡ ዓለም ጋር ጤናማ፣ የተስተካከለና ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳትመሠርት ጋሬጣ ሆኖባት ኖሯል፡፡ አሁን በተከሰቱት መልካም ለውጦች የተነሳ መልካም ጅምሮች ታይተዋል፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ ከሁለት ዓመት በኋላ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ ወደ እስራኤል ተጉዘው በርካታ ፕሮቶኮሎች መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡ ጉብኝቱ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ ሳይሆን አይቀርም፡፡
አፄ ኃይለ ሥላሴ እንኳን ወደ እስራኤል የተጓዙት በፋሽስት ወረራ ወቅት ኢየሩሳለም ውስጥ በስደት ለአንድ ዓመት በተቀመጡበት ጊዜ ነው፡፡ የአቶ ታምራት ላይኔ ጉብኝት የመጀመሪያው ምዕራፍ ከፋች ነበር፡፡ የነበረውን የዲፕሎማሲ ችግር ሙሉ በሙሉ የሰበረ ነው፡፡ ከኢትዮጵያዊ አጋር ጋር በግልጽ በአደባባይ ስለአገሮቹ ግንኙነት መነጋገር ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ እንግዲህ ኢትዮጵያንና እስራኤልን የሚያስተሳስራቸው ነገር ሌሎች አገሮች ከሚያስተሳስራቸው የሰላምና የዕድገት ጉዳዮች የተለየ ሊሆን አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ ከእስራኤል የምትፈልጋቸው በርካታ የእርሻ፣ የቴክኒክ፣ የትምህርት፣ የሕክምናና የወታደራዊ ድጋፎች ተጠናክረው መጀመር አለባቸው፡፡ 


ንጭ ሪፖርተር ጋዜጣ (እሑድ የካቲት 24 ቀን 2005 ዓም)
ተጻፈ  ክፍለጽዮን ማሞ ክፍለጽዮን ማሞ  
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው kmd_99@hotmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡   




No comments:

Post a Comment