የአዕምሮ ዝግመት ችግር (ኦቲዝም) ምንድን ነው
?
በእስራኤል ሀገር ከሚወለዱ ከመቶ ህጻናት መካከል አንዱ በአዕምሮ ዝግመት ችግር በኦቲዝም የተጠቃ ነው።
ከአስር ዓመት በፊት (እአአ በ2003 ዓም) በወጣ መረጃ በወቅቱ ከሁለት መቶ እስራኤላውያን ልጆች መካከል አንዱ በኦቲዝም ችግር የሚሰቃይ ነበር።
ኦቲዝም የአዕምሮ እድገት መዛባት የሚያስከትለው የማኅበራዊ ግንኙነትና መግባባት እክል ሲሆን ይህ እክል የአንጐልን የሥራ ሂደት በማወክ በአንጐላችን የሚከናወን የመረጃ አጠቃቀምን ያዛባል፡፡የኦቲዝምን መንስኤ ለማወቅ ብዙ ጥረት ቢደረግም እስከዛሬ ድረስ ስለ መንስኤውና መፍትሔው በእርግጠኝነት ለመናገር አልተቻለም፡፡ ከእኛ ኅብረተሰብ መካከል ብዙ ሰዎች ከዚህ የአዕምሮ ዝግመት ችግር ጋር አብረው ይኖራሉ፡፡ የዛሬን አያድርገውና እነዚህ ወገኖቻችን ከቤት እንዳይወጡና ከሰው ጋር እንዳይገኛኙ ይደረጉ ነበር፡፡ ወላጆች ቢሆኑ የልጆቻቸውን የወደፊት ሕይወት ከማመቻቸት ይልቅ እራሳቸውን በተለያዩ ሆላ ቀር አመለካከቶች በመተብተብ ("ልጄ እንዲህ የሆነው፦ ብረገም ነው፣ ኃጥያቴ ነው፣ የቤት ጣጣ ስላለብኝ ነው " በማለት) ከሰው ሲያሸሻቸውና ሲያሸማቅቃቸው ነበር፡፡ዛሬም ቢሆን በባለሞያዎች ለችግሩ ቋሚ መፍትሔ ሊገኝ አልተቻለም፤ ቢሆንም የችግሩ ተጠቂዎችን በልዩ ልዩ የትምህርት ዘዴና እንክብካቤ ለውጥ እንዲያመጡ ማድረግ እየተቻለ ነው። አንዳንድ ጥናቶች ለኦቲዝም መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ ብለው ካስቀመጧቸው ነጥቦች ለመጥቀስ ያህል:-
·
አካባቢ በመርዛማ ኬሚካሎች መበከል፣
·
በእርግዝናና በወሊድ ወቅት የሚፈጠሩ ኢንፌክሽኖች፣
·
በአንጐል ውስጥ የሚገኝ የኬሚካል መጠን መዛባትና የሆርሞን አለመስተካከል፣
·
በዘር የሚተላለፍ መሆኑና
·
በህፃናት አስተዳደግ ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ነገሮች የሚሉት ይገኙበታል፡፡
ኦቲዝም/የአዕምሮ ዝግመት ችግር/ ከሩቅ ሲያዩት የኛን ቤት የማያንኳኳ ችግር ሊመስል ይችላል፡፡ የችግሩ ተጠቂ ቤተሰቦችም ሆኑ የችግሩ ተጠቂ ህፃናት አንዳች ሰማያዊ ቁጣ /እርግማን/ ያለባቸው እንጂ ተራ የጤና እክል እንደገጠማቸው ላናስብም እንችል ይሆናል...፡፡ ይሁን እንጂ የኦቲዝም / የአዕምሮ ዝግመት/ ችግር ነገ በምንወልዳቸው ልጆች ላይ ላለመከሰቱ እርግጠኞች ልንሆን አይችልም፡፡
ህፃናት ከስድስት ወር ጀምሮ እስከ ሶስት ዓመት ዕድሜያቸው ድረስ የዚህ ችግር ተጠቂ መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን ችግሩ የሚታወቀው ህፃኑ በሚያሳየው ባህርይና ሁኔታ እንጂ በሌላ የምርመራ ዘዴ አይደለም፡፡ ይሄም በህፃኑ ላይ ችግሩ ሳይታወቅ እንዲቆይ ያደርገዋል፡፡ ኦቲዝም ራሱን ችሎ ወይንም ከሌሎች ችግሮች ጋር በተጓዳኝነት የሚመጣ ሲሆን ከዚህ ችግር ጋር አብዛኛውን ጊዜ የሚጥል በሽታና መስማት የተሳነው መሆን ጐልቶ እንደሚታይ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ የአዕምሮ ዝግመት ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች በወቅቱ ተገቢውን ክትትልና
እንክብካቤ ካልተደረገላቸው ችግሩ እየተባባሰ የመምጣት ዕድሉም ሰፊ ነው፡፡በተለይ በህብረተሰባችን ዘንድ በኦቲዝም ዙሪያ በርካታ የተሳሳቱ አመለካከቶች ሲኖሩ ከእነዚህም ጥቂቶቹ ኦቲስቲክ ልጆች አደገኞች ናቸው ብሎ ማሰብ፣ ፈፅሞ ሊሻሻሉ እንደማይችሉ ማሰብ ዋነኞቹ ሲሆኑ ኦቲስቲክ ሰዎች የሰው አይን እያዩ አያወሩም፣ ሁሉም በአዕምሯቸው ምጡቅ /ጂኒየስ/ ናቸው፣ ማውራት አይችሉምና የመሳሰሉት አስተሳሰቦች ለችግሩ ተጠቂዎች እንክብካቤና ፍቅርን እንዳንሰጥ መሰናከል የሆኑ ጉዳዮች ናቸው ።
ይሁን እንጂ ኦቲዝም በራሱ በሽታ ሳይሆን የተለያዩ ጥምር የህመም አይነቶች ከሰው ልጅ ተለምዷዊ የአኗኗር ፀባይ ወጣ ያለ ፀባይ እንዲኖረን ሲያደርጉ የሚከሰት ችግር ነው፡፡ በተጠቂዎቹ ላይ ከሚታዩት የተለያዩ ስሜቶች አንፃር ችግሩ ዝብርቅርቅ ያለ ቢመስልም ጊዜ ሰጥተን ካጠናነው መረዳቱ ብዙም አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ ከኦቲስቲኮች 90 ከመቶ ያህሉ እንደ ጤናማ ሰዎች ህይወታቸው ወደ ውጭ ሳይሆን ወደ ውስጣቸው በመንፀባረቁ እንደሌሎቻችን ሙሉ ኑሮ የማይኖሩ ቢመስሉንም ይህ አስተሳሰብ ፈፅሞ ስህተት መሆኑን ጥናቶች ያመለክታሉ፡ ፡
አንድ በኦቲዝም የተጠቃ ልጅ ከሌላው ኦቲስቲክ ልጅ የተለየ ባህሪ ሊኖረው ስለሚችል በጠቅላላው ኦቲስቲክ የሆኑ ልጆች እንዲህ አይነት ናቸው ብሎ ለመደምደምም አስቸጋሪ ነው፡፡በመሆኑም እያንዳንዱ በኦቲስቲክ የተጠቃ ሰው ፀባይ በቅርበት ማጥናት ልጁን ለመንከባከብም ሆነ ትምህርት ለመስጠት ዋነኛ አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡የኦቲዝም ችግር ያለባቸው ልጆች ከሚያሳዩዋቸው ባህርያት መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፦
§ በራሳቸው ዓለም የሚኖሩ በመሆኑ ሌላውን ለማወቅ ፍላጐት የላቸውም
§ ቃላት አውጥቶ መነጋገርና መግባባት ያቅታቸዋል
§ ሌሎች የተናገሩትን መደጋገም ይወዳሉ
§ የሰሙትን ቃል /ዐረፍተ ነገር/ በሰሙት ድምፅና ቅላፄ መሠረት ደግመው መናገር ይችላሉ
§ በእናቶቻቸውም ሆነ በሌላ ሰው መታቀፍንና መነካትን አይፈልጉም
§ መኪና፣ ገደል፣ ፎቅ፣ ፈፅሞ አይፈሩም
§ ራሳቸውን ከግድግዳና ከሌሎች ግዑዝ ነገሮች ጋር በተደጋጋሚ ያጋጫሉ፤
§ እጃቸውን ይነክሳሉ፤ ፊታቸውን ይቧጭራሉ
§ የመንቀዥቀዥ የመቁነጥነጥ ባህርይን ያሳያሉ
§ ድንገት ስሜታቸው ይለዋወጣል፡፡ ከት ብለው ሊስቁ ወይንም ስቅስቅ ብለው ሊያለቅሱ ይችላሉ
§ አብዛኛዎቹ የምግብ አበላል፣ የመፀዳጃ ቤት አጠቃቀምና የአለባበስ ሥርዓትን አያውቁም
§ በጣም ረዥም ነገሮች ላይ መንጠልጠል፣ መዝለል ይወዳሉ
§ በአንዳንድ ነገሮች ላይ በጣም ፍርሃት ሲያሳዩ በሌላው ደግም የሚያስደንቅ ድፍረት ይኖራቸዋል፡፡ ለምሳሌ ከፊታቸው የቆመን ትልቅ ነገር ተጋጭተው ሲያልፉት በጣም ጥቃቅን የሆኑ ነገሮች እንዳይገጯቸው ሲጠነቀቁና ሲፈሩ ይስተዋላሉ፡፡
የኦቲዝም ችግር ተጠቂ የሆኑ ልጆች፤ በአካላቸውና በገፅታቸው ላይ ምንም አይነት ለውጥ ስለማይኖራቸው፣ ችግራቸውን ቶሎ ለመረዳትና ተገቢ እንክብካቤ ለማድረግ አስቸጋሪ ይሆናሉ፡፡ ችግሩ ሁነኛና ዘላቂ ፈውስ ያልተገኘለት ቢሆንም የችግሩ ተጠቂዎችን በልዩ ስልጠና እና እንክብካቤ ለተሻለ ህይወት ማብቃት ይቻላል፡፡ ኦቲስቲክ ከሆኑ ሰዎች መካከልም እጅግ ከፍተኛ ብቃትና ልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ሰዎች እንደነበሩ የታሪክ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

No comments:
Post a Comment