Sunday, February 17, 2013

አይሁዳዊያን መጻሕፍት





              አይሁዳዊያን  መጻሕፍት

    አይሁዳዊያን በትውፊት ከቀደሙ አባቶቻቸው የወረሷቸው ሁለት አይነት ሃይማኖታዊ መጻሕፍት አሏቸው። የመጀመሪያዎቹ በጽሁፍ ተዘጋጅተው ከቀድሞ አባቶቻቸው የተረከቡት መጻሕፍት ሲሆኑ በዕብራይስጥ "ቶራ ሼ-በክታቭ" ይባላሉ ለምሳሌ ያህል አምስቱ የሙሴ መጽሐፍት ናቸው። ሁለተኞቹ ከቀድሞ አባቶች በትውፊት በቃል የተረከቡት መጻሕፍት ናቸው በዕብራይስጥ "ቶራ ሼ-በአልፔ" ይባላሉ ለምሳሌ  ያህልም የ"ታልሙድ" እና የ"ሚድራሽ" መጻሕፍት ናቸው።

ታልሙድ (תַּלְמוד)

   በአምስቱ የሙሴ መጽሐፍት የተጻፉ አድርግና አታድርግ የሚሉትን ትእዛዝ የሚተሮግምና የሚያብራራ  የቶራ ሼ-በአልፔ መጽሐፍ ሲሆን ይህ መጽሐፍ የአይሁድ ታላላቅ ራባዮች (ራባናት- የአይሁድ መምህራን) ለተማሪዎቻቸው በተለያየ ጊዜ የኦሪት ህግጋትን በተመለከተ ያስተማሮቸው ትምህርቶች የያዘ ነው። ይህም ትምህርት ከትውልድ ትውልድ በቃል ሲወርድ-ሲዋረድ ቆይቶ ራባዮች በቃል የሰሟቸውን  "በቃል ያለ ይረሳል በጽሑፍ ያለ ይወረሳል" እንደሚባለው እንዳይረሳ እነዚህን ትውፊታዊ ትምህርቶች ጻፎቸው። እነዚህንም በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሊቀ ራባናት ይሁዳ  ሃነሲ ተሰብስቦ ተጠረዘ ። ራብ ይሁዳ እነዚህን የታልሙድ ጥራዛት ሲያዘጋጃቸው በስድስት ክፍሎች ("ሺሻ ሴዴሪም"  (six orders)) ከፋፍሎ ነው ። እነዚህም የታልሙድ ስብስቦች ሚሽናህ  ተብለው ይጠራሉ። 




ሚሽናህ (משנה)

    ሚሽናህ የሚለው ስያሜ ሻናህ (ከለሰ ፣ ደገመ) ከሚለው የዕብራይስጥ ግስ የተገኘ ቃል ሲሆን ፤ ሚሽናህ ማለት መከለስ መድገም ማለት ነው። ራባይ ይሁዳ  ሃነሲ በ220 ዓም በቃል የነበሩት የኦሪ ትምህትቶችን አሰባስቦ ለመጀመሪያ ጊዜ በጥራዝ አዘጋጅቶታል። ሚሽናህ የታልሙድ ክፍል ሲሆን ፤ በእያንዳንዱ የሚሽናህ ትርጓሜ ትምህርቶች ላይ ራባናት ተከራክረውና ተወያይተው የወሰኑት የመጨረሻ የመደምደምያ ትምህርታቸውን አስፍረዋል ፤ ይህም በዕብራይስጥ "ግማራ" ይባላል።


ታናህ የአይሁዳዊያን መጽሐፍ ቅዱስ ሲሆን በውስጡ ሶስት የቅዱሳት መጻሕፍት ስብስብ ይዟል፤ እነርሱም ቶራ፣ንቪኢም እና ክቱቪም ናቸው

ቶራ (תּוֹרָה)  
    ቶራ የቃሉ ትርጓሜ መራ ፣አዘዘ እንደማለት ነው። መጽሐፈ ቶራ የአይሁዳዊያን ታላቅ መጽሐፍ ሲሆኑ፤ የታናህ የመጀመሪያው ክፍልም ነው። መጽሐፈ ቶራ አምስቱ የሙሴ መጻሕፍትን አጠቃሎ የያዘ ነው ። አምስቱ የሙሴ መጻሕፍት የሚባሉትም ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ናቸው ፦
א.       ኦሪት ዘፍጥረት  (በዕብራይስጥ ቋንቋ  "በሬሼት בראשית " ተብሎ ይጠራል )
ב.       ኦሪት ዘጸአት  (በዕብራይስጥ ቋንቋ  "ሼሞት שמות "  ተብሎ ይጠራል  )
ג.        ኦሪት ዘኁልቁ (በዕብራይስጥ ቋንቋ  "ቨዪክራ ויקרא " ተብሎ ይጠራል  )
ד.        ኦሪት ዘሌዋውያን (በዕብራይስጥ ቋንቋ  "በሚድባር במדבר " ተብሎ ይጠራል  )
ה.       ኦሪት ዘዳግም  (በዕብራይስጥ ቋንቋ  "ዴቫሪም דברים "ተብሎ ይጠራል )
ቪኢም (נְבִיאִים) 
   ንቪኢም ማለት የቃሉ ትርጉም ነብያት ማለት ነው። መጽሐፈ ንቪኢም ሁለተኛው የታናህ ወይም የአይሁድ መጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሲሆን የነብያት ትንቢታቸው የሰፈረበት መጽሐፍ ነው። መጽሐፈ ንቪኢም ሁለት ክፍሎች ሲኖሩት መጽሐፈ ኢያሱ፣ መጽሐፈ መሳፍንት፣ መጽሐፈ ሳሙኤልና መጽሐፈ ነገስት ባንድላይ "ንቪኢም ርሾኒም" (የመጀመሪያውያዎቹ ነብያት) መጽሐፍት ሲባሉ፤ እንዲሁም ትንቢተ ኢሳያስ፣ትንቢተ ኤርምያስ፣ ትንቢተ ሕዝቅኤልና አስራ ሁለቱ ንዑሳን ነብያት "ንቪኢም አሀሮኒም" (የመጨረሻዎቹ ነብያት) የጻፎቸው መጽሐፍት ናቸው። መጽሐፈ ንቪኢም ተብለው የሚጠሩት ባጠቃላይ  የሚከተሉት ናቸው ፦
1.    መጽሐፈ ኢያሱ
2.   መጽሐፈ መሳፍንት
3.   መጽሐፈ ሳሙኤል
4.   መጽሐፈ ነገሥት
5.   መጽሐፈ መክብብ  
6.   ትንቢተ ኢሳያስ
7.   ትንቢተ ኤርምያስ
8.   ትንቢተ ሕዝቅኤል
9.   ትንቢተ ሆሴዕ
10.  ትንቢተ ኢዩኤል
11.   ትንቢተ አሞጽ
12.  ትንቢተ አብድዩ
13.  ትንቢተ ዮናስ
14.  ትንቢተ ሚክያስ
15.  ትንቢተ ናሆም
16. ትንቢተ ዕንባቆም
17.  ትንቢተ ሶፎንያስ
18.  ንቢተ ሐጌ
19.  ትንቢተ ዘካርያስ
20. ትንቢተ ሚልክያስ ቸው።


ክቱቪም (כְּתוּבִים)
    ክቱቪም ማለት መልእክታት ወይም ጽሑፎች ማለት ነው። ክቱቪም ሶስተኛውና የመጨረሻው የአይሁድ መጽሐፍ ቅዱስ (የታናህ) ክፍል ሲሆን ይህን መጽሐፍ የተለያዩ የእግዚአብሔር ሰዎች የከተቧቸው መጽሐፍት ናቸው ። የክቱቪም መጻሕፍት የሚከተሉት ናቸው ፦
§  መጽሐፈ ኢዮብ
§  መዝሙረ ዳዊት
§  መጽሐፈ ምሳሌ
§  መኃልዬ መኃልይ ዘሰለሞን
§  መጽሐፈ ሩት
§  ሰቆቃው ኤርምያስ
§  መጽሐፈ መክብብ
§  መጽሐፈ አስቴር
§  ትንቢተ ዳንኤል
§  መጽሐፈ ዕዝራ
§  መጽሐፈ ነህምያ
§  መጽሐፈ ዜና ናቸው።



















Saturday, February 16, 2013

" የኩሽ ፈርጦች "

                       የእስራኤልኩሽሞች” ”
           ሑፍ ተጋንኗል !


       ለእዚህ መጣጥፌ ምክንያት የሆነኝ ባለፈው ሳምንት በእስራኤል የሚኖሩ ቤተ እስራኤላውያን በተመለከተ “ የእስራኤል “ኩሽሞች” (ባሪያዎች) ” በሚል ርዕስ አልአዛር ኬ የተባሉ ሰው የጻፉት ፅሁፍ ነው ። ፈላሻ ማለት ፈለሰ ከሚለው የግእዝ ግስ የተገኘ ቃል ሲሆን የሰው ልጅ ደግሞ ሀገሩን ለቆ የሚፈልሰው ወይም የሚሰደደው ወዶ ሳይሆን በሀገሩ ጦርነት ሲነሳ፣ የኑሮ ሁናቴ አልስተካከል ሲል ወይም በሌሎች ችግሮች ነው። ታዲያ ቤተ እስራኤላውያን ወደ ሀገራችን ገቡ የሚባሉት ቀዳማዊ ምኒሊክ አባቱ ንጉሥ ሰሎሞን ዘንድ ቆይቶ ሲመለስ ብዛት ያላቸው ቤተ-እሥራኤላውያን ተከትለውት ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡ “ክብረ ነገስት” የሚባለው ጥንታዊ መጽሐፍ ይገልፃል። ራሳቸው ቤተእስራኤላውያንም በአፈታሪክ የሰሙትን ሲናገሩ ይደመጣሉ። ከዛም በኋላ በባቢሎን ምርኮ ጊዜ ወደ ግብጽ ከተሰደዱት እስራኤላውያን ከፍለው ወደ ኢትዮጵያ እንደገቡ አንዳንድ ሰዎች ይናገራሉ ፤ ከዚያም ጊዜ ጀምሮ ቤተ-እስራኤላውያን በኢትዮጵያ ይኖሩ ነበር ።ኢትዮጵያዊያንም እነዚህን ማኅበረሰብ ከሀገራቸውን ርቀው ተሰደው የሚኖሩ ለማለት “ፈላሻ ፤ ፈላሾች” ይሏቸዋል። ልክ እስራኤላውያን በሀገራቸው ተሰደው የሚኖሩትን ሰዎች “ዖቭደይ ዛሪም” እንደሚሏቸው ማለት ነው። አንዳንድ ሰዎች ግን “ፈላሻ” የሚለውን ቃል እንደ ስድብ ሲጠቀሙበት ይሰማል።(የተጠቀምኩበት ዘመን በጠቅላላ እ.ኤ.አ ነው)

        እንደሚታወቀው ከዛሬ 30 ዓመት በፊት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የኢትዮጵያ ይሁዳዊያን ወደ እምነት ሀገራቸው እስራኤል በየጊዜው ይጓዛሉ። ባለፉት ሶስት ዓመታት እንኳን ከኢትዮጵያ ወደ እስራኤል የተጓዙትን ቤተ-እስራኤላዊያን ብዛት ብንመለከት፣ በ2010 ዓ.ም 1,652፣ በ2011 ዓ.ም 2,666 እና በ2012 ዓ.ም 2,355 ቤተእስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድራቸው ተጉዘዋል ። በአሁኑ ጊዜ የሀገሪቱ የህዝብ ብዛት ከ7.9 ሚልዮን በላይ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ወደ 124 ሺ ያህሉ ቤተ-እስራኤላውያን ናቸው።ለመጀመሪያ ጊዜ ብዛት ያላቸው ቤተ-እስራኤላዊያን ከ1981 ዓ.ም እስከ 1984 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ከጎንደርና ከትግራይ አካባቢዎች ተነስተው ወደ ሱዳን ተጓዙ፤ ታዲያ እነዚህ ሰዎች እስራኤል እስኪደርሱ ብዙ መስዋዕትነት ከፍለዋል፤ የተወለዱበትና የአደጉበትን ቀዬ ትተው፣ ወልደውና ከብደው ከኖሩበት መንደራቸው ተነጥለው፣ ለስንቅና ለችግር ብለው የያዙትን ጥሪት በዘራፊዎች ተነጥቀው፣ በደዌና በረሃብ ልጆቻቸውንና ወላጆቻቸውን ያጡትን ቤቱ ይቁጠረው።
(አራት ሺህ የሚጠጉ ቤተ-እስራኤላውያን በሱዳን ምድር በረሃብና በበሽታ እንዳለቁ ቤተ-እስራኤላውያን ይናገራሉ)ታዲያ ያንን ሁሉ አልፈው እስራኤል ሲደርሱ ቋንቋው፣ ባህሉ፣ የሀገሪቱ ሕግ፣ የልጅ አስተዳደጉ፣ ለዛውም የሚያውቁትና ያደጉበት የቶራ ህግ (የኦሪት ህግ) እንኳን ሳይቀር የ”ግማራ” እና የ”ሚሽናህ” ትምህርት ተጨማምሮበት ብዙው ነገር ለእነርሱ አዲስ ነበር ። ቢሆንም ግን ቀስ በቀስ እንቁላል በእግሯ ትሄዳለች እንደሚባለው ከነጭ አይሁዳዊያን ጋር ተዛንቀው መኖር ጀመሩ። ይህን ስል ግን አብዛኛው እድሜው ገፍቶ ከኢትዮጵያ የሄደው ሰው እስካሁን ድረስ የሀገሪቱን ቋንቋና ባህል መልመድ እንደተሳነው እሙን ነው።(ይህ ችግር አሁን በቅርቡ የሄዱትንም ያጠቃልላል)። ይህም ቢሆን የእስራኤል መንግስትም ሆነ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ህዝቡን ከመርዳትና ከማስተማር አልቦዘኑም። ምንም እንኳን የተለያዩ ችግሮች በእስራኤል ቢኖርባቸውም አቶ አልአዛ ያዩበት መነጽር እኔ በቅርበት ከማየው ጋር አልተስማማልኝም።

         በመጀመሪያ አቶ አልአዛር ቤተእስራኤላዊያንን ከድሩዚም ጋር አመሳስለው ነው ያቀረቡት። ሁለቱን ህዝቦች ያመሳሰሉት ለሀገራቸውና ለህዝባቸው ታማኝ በመሆናቸው ነው። ይህ ደግሞ ነውሩነቱ ምን ላይ ነው? በመንግስት ላይ በአመጽ አለመነሳታቸው ወይስ ወደ ኢትዮጵያ መልሱን ባለማለታቸው ይሆን? ደግሞስ ይሄን ያህል የሚያማርር ነገር ምን ተገኝቶ ነው? አንድ ኅብረተሰብ በሀገሩ ጉዳይም ሆነ በራሱ ጉዳይ ያልመሰለውና የማይዋጥለት ነገር ሲኖር ሃሳቡን በጽሁፍም ሆነ በሰላማዊ ሰልፍ መግለጽ ንጹህ የዲሞክራሲ ባህል ነው። ይህን ደግሞ እርሶም ያውቁታል ብዬ አምናለሁ። እስራኤል ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ ይሁዳዊያን የሚኖሩባት የይሁዳዊያን ሀገር ናት (ዐረብ እስራኤላውያን ጨምሮ) ታዲያ በዚች ሀገር በየጊዜው የተለያዩ ኅብረተሰቦች የመንግስትን ፖሊሲ በመደገፍና በመቃወም እንዲሁም ሃሳባቸውን በሰላማዊ ሰልፍ ለመግለጽ አደባባይ ይወጣሉ። ቤተ እስራኤላውያንም የኅብረተሰቡ አንድ ክፍል እንደመሆናቸው በተለያየ ጉዳይ አደባባይ ወጥተዋል። እርሶ እንዳሉት ጠቅላላ ቤተ-እስራኤላውያንን ያነሳሳ ከ1996 ዓ.ም ለሜጌን ዳቪድ(የእስራኤል ቀይ መስቀል) የለገሱት ደም በመደፋቱ ካደረጉት ተቃውሞ ውጪ ያን ያህል የተጋነነ ነገር አልታየም። እስቲ በጽሑፍዎት ላይ ያነሷቸውን የቤተእስራኤላውያን ችግሮች በዝርዝር እንመልከት ፥ 

የቤት ግዢ

          በአሁን ሰዓት በእስራኤል የቤት ዋጋ ጣራ ነክቷል፤ ለምሳሌ አንድ መለስተኛ ባለ ሶስት ክፍል ቤት (ሁለት መኝታ ቤትና አንድ ሳሎን ያለው) ለመግዛት ከሚልዮን እስከ 1.5 ሚልዮን ሼቄል(የእስራኤል መገበያያ ገንዘብ) ሲያስፈልግ፤ ይህንኑ ቤት ለመከራየት ደግሞ ከ2800 እስከ 4000 ሼቄል በወር ያስከፍላል። በዚህም ምክንያት አብዛኛው በመካከለኛ ኑሮ የሚገኝ እስራኤላዊ ቤት መግዛት ተስኖታል። ኢትዮጵያዊያን አዲስ ገቢዎች ደግሞ አመትና ሁለት አመት በ”መርካዝ ክሊታ”(ጊዜያዊ መጠለያ) ቆይተው ቤት ይገዛሉ። ለቤት መግዣ የሚቀበሉት ገንዘብ በስጦታና የተወሰነው በብድር ሲሆን፤መጠኑም የሚወሰነው እንደ ቤተሰባቸው ብዛት ነው። የሚገዙት ቤት እንደ ቤተሰባቸው ቁጥር ማብሰያ፣ መታጠብያና መጸዳጃ ክፍሎችን ሳይጨምር ሶስትና ከሶስት ክፍል በላይ ነው።እውነት ለመናገር አብዛኛው ኢትዮጵያውያን አዲስ ገቢዎች (ቤተእስራኤላውያን) ቤት ለገዙበት ብድር በወር ለባንክ የሚከፍሉት ሶስትና አራት ቀን ሰርተው ያገኙታል። ይህን ቤት ግን እንከራይ ቢሉ በወር የወር ደሞዛቸውን 75% ይከፍሉ ነበር ።

          ሌላው “ቤት ሲገዙ አንድ ቦታ እንዲገዙ ይገደዳሉ” ብለው አቶ አላዛር ያነሱት ፈጽሞ ከእውነት የራቀ ሲሆን እራሳቸው ቤተ-እስራኤላውያን ግን ቤት ሲገዙ ለለቅሶም፣ ለድግሱም፣ ቡና ለመጠጣጣትም ጭምር ሲሉ ተፈላልገው አንድ አካባቢ ይመርጣሉ። ይህን ጉዳይ የእስራኤል የአዲስ ገቢዎች መስሪያ ቤት በጥብቅ እንደሚቃወመው የአደባባይ ምስጢር ነው። ይህም ሆኖ የከተማው አዲስ ገቢ ኢትዮጵያዊያንን የመቀበል ኮታው እስኪሞላ ድረስ እነርሱ ራሳቸው የፈለጉት ቦታ መርጠው ይገዛሉ። በዚህም ምክንያት ነው ቤተ-እስራኤላውያን በአንድ ቦታና ከተማ በብዛት ተሰባስበው የሚኖሩት። በ1985 የአይሁዳዊያን አዲስ ገቢዎች መስሪያ ቤት ወደ እስራኤል የሚገቡ ቤተእስራኤላውያን በ25 የተለያዩ ስፍራዎች ቤት ገዝተውም ይሁን የአሚዳር ቤት (የመንግስት የኪራይ ቤቶች) ተቀብለው እንዲኖሩ ሲያደርጋቸው ከእያንዳንዱ የከተማዋ ነዋሪዎች ብዛት አንጻር የቤተእስራኤላውያን ቁጥር ከ2% እና 4% በላይ እንዳይሆን ወስኖ ነበር፤ በ2010 ዓ.ም በወጣው መረጃ መሰረት ግን ቤተ-እስራኤላውያን በክርያት-መልሂ ፣ በአፉላና በያቭኔ ከተሞች ነዋሪዎች መካከል ከሰባት እስከ አስራ አምስት ከመቶ የሚሆን ቁጥር ነበራቸው። ይህ ማለት ግን በከተማው ከሚኖረው ከሌላው የእስራኤል ማኅበረሰብ አንጻር እንጂ ቤተ-እስራኤላውያን በብዛት የሚኖሩባቸው ከተሞች ናታንያ፣ አሽዶድ፣ ሪሾን ለጽዮን፣ ሮሆቮት፣ ኢየሩሳሌምና የመሳሰሉ ናቸው።አብዛኞቹ ላጤ ቤተእስራኤላውያን የማሽካንታ ተቋዳሽ አይደሉም። እንደማንኛውም እስራኤላዊ እንዲገዙ በመንግስት ተወስኖ ከሰሩና መግዛት ለሚፈልጉት ቤት 30% የቤት መግዣ ገንዘብ ካላቸው የተቀረውን ከባንክ መበደር ይችላሉ። ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ግን እንደወገኖቻቸው እነርሱም ገንዘብ ተሰጥቷቸው ይገዙ ነበር። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ አቶ አልአዛር፣ ቤተእስራኤላውያን የሚገዙት ቤት ሁለት ክፍል ብቻ እንደሆነና አንድ አካባቢ እንዲገዙ እንደሚገደዱ ከመግለፃቸውም ባሻገር “ሁሉም በብድር ያገኙትን ገንዘብ ይዘው ያመሩት ርካሽ የመኖሪያ ቤቶች ወደሚሸጡባቸው፣ ምንም አይነት የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች ባልተዘረጉባቸው ኋላቀርና ጭራሹኑ ወደተዘነጉት አካባቢዎች ነበር፡፡” ብለዋል።እንዲህ ማለታቸው የሚያሳፍር ነው። ለመሆኑ አቶ አላዛር የሚሏቸው አካባቢዎች የትኞቹ ናቸው? አፉላን፣ ክርያት መላኺን፣ ክርያት ጋትን፣ ዖር ይሁዳን የመሳሰሉትን ከተሞች ማለታቸው ይሆን? አቶ አልአዛር የመሰረተ ልማት አገልግሎት ያልተዘረጋባቸው ሲሉ ስልክ፣ ጋዝ፣ ውሃ፣ መብራት ያልገባላቸው ቤቶች የተገነቡባቸው ማለታቸው ነው ወይስ መንገድና የህዝብ ማጓጓዣ የሌለባቸው ከተሞች ለማለት ነው፤ አሊያስ ለልጆች መጫወቻ ስፍራና ትምህርት ቤት የሌለባቸው መንደሮች ማለታቸው ነው? ለማንኛውም ስለከተሞቹ የማያውቁ ከሆነ ጎግልን ይጠይቁ። በዛውም ስለነዋሪዋቻቸውም ይመልከቱ።

ኩሺም ተብለው መጠራታቸው

          ሌላው ቤተእስራኤላውያን ኩሽ ወይም ኩሺም ተብለው ስለመጠራታቸው (ስለመሰደባቸው) አንስተዋል ። በዕብራይስጥ ቋንቋ ኩሽ ማለት ባርያ ማለት ሲሆን ኩሺም ደግሞ ባርያዎች ማለት ነው። ሌላው ኩሽ ስንል የኖህ የልጅ ልጆች ምድርን ሲከፋፈሉ ከምጽራይም (ከግብጽ) በታች በስተደቡብ ባለው ስፍራ የኩሽ ልጆች እንደሰፈሩና ምድሪቱም የኩሽ ምድር ተብላ ትጠራ እንደነበር መጻህፍት ይናገራሉ። በዚህም መሰረት እኛ አበሾች የኩሽ ልጆች ነን።ሌላው በዕብራይስጡ ቶራ (ኦሪት) ላይ እንደተጻፈው የታላቁ ነብይ ሙሼ (ሙሴ) ሚስት ኩሺ እንደነበረች ይናገራል። ኩሺ መባልዋ በኩሽ ምድር የተወለደች ኩሺት ስለሆነች ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ እስራኤላዊ ራብ (የኦሪት ምምህር) ባንድ ወቅት ያለኝን ላነሳ እወዳለሁ “የሙሼ ራቤኑ ሚስቱ እንዳንተ ኩሺ ነበረች “ ብሎኛል። ይህን ማለቱ እኔ እንደሚገባኝ እንዳንተ ጥቁር ነበረች ለማለት ነው። ይህ ራብ የሙሴ እህት ሜርያም (ማርያም) ሙሴ ኩሺት ኢትዮጵያዊት በማግባቱ ብትቃወም የደረሰባትን ስለሚያውቅ በዚህ ጉዳይ እኔ ላይ እንደማይቀልድ አውቃለሁ። ዛሬ በአማርኛም ሆነ በሌሎች ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል በእናት ቋንቋው በዕብራይስጥ ላይ ብንመለከት “ኩሽ፣ የኩሽ ምድር” እያለ ነው የሚያስቀምጠው።ታዲያ ዛሬ ነጭ እስራኤላውያን ቤተ እስራኤላውያንን “ኩሺ” ብለው መጥራታቸው ጥቁሮች ወይም ኢትዮጵያዊ ለማለት ነው። እኛም እኮ ነጭ ስናይ “ፈረንጅ”፤ ጥቁር አፍሪካዊያንን ደግሞ ስናይ “ኔግሮ” እንደምንለው ነው። ለአብዛኞቹ እስራኤላውያን ኩሺ ማለት ጥቁር ማለት ነው።

የሞያና የክህሎት ስልጠና

          እስራኤል ውስጥ ወደ ዘጠኝ የሚሆኑ ዩንቨርስቲዎችና 49 ኮሌጆች ይገኛሉ። አብዛኞቹ እስራኤላውያን የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው፤ ይህ ግን ለአብዛኛው ኅብረተሰብ ሥራ ለመያዝ፣ ተፎካካሪ ለመሆንና ቤተሰብ ለማስተዳደር ብቁ አያደርጋቸውም። የሀገሪቱ ተጨባጭ ሁናቴ እንዲህ በሆነበትም፣ በጣት የሚቆጠሩ ቤተእስራኤላውያን ለመጀመርያም ሆነ ለሁለተኛ ዲግሪ በዩንቨርስቲዎችም ሆነ በኮሌጆች ገብተው ይማራሉ። በ2011 ዓ.ም በክነሴት (በእስራኤል ፓርላማ) በቀረበ አንድ ሪፖርት፤ ከእስራኤላውያን የከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎች መካከል የቤተእስራኤላዊያን ተማሪዎች ብዛት 8% ብቻ ነበር። በ2009 ዓ.ም የቤተእስራኤላውያን ከፍተኛ ተቋም ተማሪዎች ብዛት 1921 የነበረ ሲሆን ፤ ይህ ከጠቅላላው ካገሪቱ የከፍተኛ ተቋም ተማሪዎች 0.9% ነበር። የ2005 እና የ2009 ሲነጻጸር የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ከ155 ወደ 298 ጨምረዋል።
ያለፈው አመትን ሳይጨምር በጠቅላላው 2060 ቤተእስራኤላውያን የከፍተኛ ተቋማት ተመራቂዎች ሲኖሩ፤ ከነሱም 88% የመጀመሪያ ዲግሪ ሲሆን የተቀሩት ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው ናቸው። በሳይንስ፣በህክምና፣በእርሻ፣በቋንቋና በመሳሰሉት የትምህርት ዘርፎች ላይ ብዙ ቤተእስራኤላውያን ሲሳተፉ አይታዩም። ይህም የሆነው የመግቢያ መስፈርቱን ብዙዎች ስለማያሟሉ ነው ።ሌላው የአጭርና የረዥም ጊዜ የሞያ ስልጠና እየወሰዱ የተወሰኑት በሰለጠኑበት ሞያ ተሰማርተው ይገኛሉ። አቶ አልአዛር ኬ እንዳሉት የነርሲንግ፣ የልብስ ስፌት፣ የብረታብረትና የእንጨት ሥራ በመሳሰሉት እንዲሰለጥኑ ይደረጋሉ። በዚህም በሰለጠኑበት የተወሰኑት በስራ ላይ ቢሰማሩም፤ ይህ በቂ ነው ማለት አይደለም። ቢሆንም ግን ከሌላ ሀገር ከሚመጡ አዲስ ገቢ ይሁዳዊያንና አረብ እስራኤላውያን ጋር ተወዳድረው ስለሆነ መፍረድ አይቻልም። ለዛውም ሌሎቹ ከመጡበት ሀገር የስራ ልምድ ይኖራቸዋል። መቼም መንግስት ቤተእስራኤላውያን ብቻ ሰልጥነው የሚሰሩበት የስራ ዘርፍ ይፍጠር አልያም ሌሎቹን ወደጎን አድርጎ የእነርሱን ብቻ ይመልከት ማለት አይቻልም። በዚህም ላይ አብዛኞቹ ከመማር ይልቅ ኬሴፍ (ገንዘብ) ወደሚያገኙበት ሥራ መሰማራት ይቀላቸዋል። እኔ እንደማስበውና በገሃድም እንደሚታየው የቤተእስራኤላውያን ችግር ምንጮች ነጭ ይሁዳውያን ሳይሆኑ(የተወሰኑ ዘረኞች ቢኖሩም እንኳን) ራሳቸው ቤተእስራኤላውያን ናቸው። ለራሳቸውም ሆነ ለሌላው ወገናቸው የችግር ምንጮች ራሳቸው ቤተእስራኤላውያን ናቸው። ወደፊት እነዚህንና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች በዝርዝር ለማንሳት እሞክራለሁኝ። እስከዛው የተዛባ መረጃ ከማስተላለፍ እንቆጠብ እያልኩኝ እሰናበታለሁኝ። ቸር ቆዩኝ።

ምንጭ፦ አዲስ አድማስ ጋዜጣ

የቤተ እስራኤላውያኑ እናቶች ማህፀን ምነው ድንገት ነጠፈ ?


       የቤተ እስራኤላውያኑ እናቶች ማህፀን
              ምነው ድንገት ነጠፈ ?
 በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት በተጋጋለበት በ1984 ዓ.ም ነበር የእስራኤል ጦር ሃይልና የስለላ ድርጅቱ ሞሳድ አስር ሺ የሚሆኑ ቤተእስራኤላውያንን፣ በሱዳን በኩል በአውሮፕላን በማጓጓዝ የዘመናት ተስፋና ጉጉታቸውን እውን ያደረጉላቸው፡፡ ይህንን ወደ ተስፋይቱ አገር የተደረገ ጉዞ (አሊያህ) ቤተእስራኤሎቹም ሆኑ የእስራኤል መንግስት “ዘመቻ ሙሴ” በሚል ስያሜ እስከዛሬ ድረስ ከፍ ባለ አድናቆት ያስታውሱታል፡፡ የእስራኤል የጦር ሀይልና የደህንነት ጐበዛዝት በ“ዘመቻ ሙሴ” አስር ሺ የሚሆኑትን ቤተእስራኤላውያን ወደ ቅድስቲቱ የተስፋዋ ሀገራቸው ማጓጓዝ ቢችሉም ልባቸው ገና ጨርሶ አላረፈም ነበር፡፡ ምነው ቢባል ዘመቻውን እያካሄዱት የነበረው የአረብ ሊግ አባል፣ እስላማዊና እንደ እስራኤል “ጠላት” ሀገር ተደርጋ በምትቆጠረው በሱዳን ውስጥ ስለነበር ነው፡፡ በዚህ የተነሳ እስራኤል ውስብስቡን “ዘመቻ ሙሴ”ን በተቻላት አቅም ሁሉ ለማፋጠን ብትሞክርም አጥብቃ የፈራችውን ነገር ማስቀረት አልቻለችም፡፡ 

      የሱዳን መንግስት ለዘመቻ ሙሴ አይቶ እንዳላየ በመሆን (በእርግጥ አብዛኛውን ነገር አያውቅም ነበር) ሲሰጥ የቆየውን ድጋፍ ማቋረጡን ያስታወቀው ድንገት ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ “ዘመቻ ሙሴ” ገና በግማሽ መንገድ ላይ እንዳለ ቀጥ አለ፡፡የሱዳን መንግስት ድንገተኛ ውሳኔ በተለይ በኢትዮጵያ ይካሄድ የነበረውን የእርስ በርስ ጦርነት ሠፊ ቀጠና በአሳር በመከራ በማለፍ በርካታ ቀናትን ከፈጀ አስቸጋሪና ፈታኝ የእግር ጉዞ በኋላ፣ ሱዳን ገብተው ለተሠባሠቡት ቤተእስራኤላውያን ዱብእዳ ብቻ ሳይሆን ልባቸውን ሊያፈርሰው የደረሰ አስደንጋጭ ጉዳይም ነበር፡፡ እናም ታዲያ አስራ አምስት ሺ የሚሆኑት ቤተእስራኤላውያን ተሠባስበውበት በነበረው የሱዳን በረሀ ላይ ለመቅረት በመገደዳቸው፣ በታናካህ ቅዱስ መጽሀፍ ውስጥ እንደተፃፈው፣ የቀደሙት አባቶቻቸው በሲናይ በረሀ ላይ ለአመታት እንደባዘኑት ሁሉ እነሱም ለአመታት መባዘን ግዴታቸው ሆነ፡፡ በዚህ ክፉ እጣ የተነሳም ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉት እንደጓጉና እንደተመኙት የልባቸው ሳይደርስ መከረኛ ህይወታቸውን ለሱዳን በረሀ ገብረዋል፡፡ በ1991 ዓ.ም ግን ለሠባት አመታት ያህል የተኛና ያንቀላፋ መስሎ የነበረው የእስራኤላውያን ጠባቂ፣ በአዲስ መንፈስ ከመቼውም በተሻለ ሁኔታ ክንዱን አፈርጥሞ ለኢትዮጵያውያን ቤተእስራኤሎች “እነሆኝ አለሁ!” አላቸው፡፡ እድሜ ዘመናቸውን ሙሉ “ለከርሞ በእየሩሳሌም እንገናኝ” ሲባባሉና አሊያሃቸውን ለመፈፀም በበረሀ ሲባዝኑ የነበሩ ከዘመቻ ሙሴ የተረፉት ቤተእስራኤላውያን “እነሆ የተስፋውን ቀን ጥበቃ ፍፃሜው አሁን ነው!” ተባሉ፡፡

      እንደተለመደው የእስራኤል መንግስት ከጦር ሀይሉ፣ ከስለላና ከደህንነት ተቋማቱ በልዩ ብቃታቸው የመለመላቸውን ጐበዛዝቱን “ዘመቻ ሶሎሞን” የሚል ስም የወጣላትን ኢትዮጵያውያን ቤተእስራኤላውያንን ወደ እስራኤል የማጓጓዝ አሊያህ እንዲያስፈጽሙ ወደ አዲስ አበባና ጐንደር በግልጽ አሠማራ፡፡ እነሱም ቀደም ብለው በተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አባልነት ተመዝግበው ለዚሁ ዘመቻ አፈፃፀም ወደ ኢትዮጵያ ከገቡት የተለያየ ዜግነት ካላቸው ይሁዲዎች ጋር በመተባበር፣ ድፍን አለሙን ሁሉ ጉድ ባስባለ ቅንጅትና ብቃት አስራ አራት ሺ ሶስት መቶ ሀያ አምስት ቤተእስራኤላውያንን ወደ እስራኤል ለማጓጓዝ ቻሉ፡፡ በ“ዘመቻ ሶሎሞን” እንደቀድሞው “ዘመቻ ሙሴ” ያለ የጉዞ መንቀራፈፍ ፈፅሞ የሚታሰብ አልነበረም፡፡ እናም እስራኤል አስራ አራት ሺ ሶስት መቶ ሀያ አምስቱን ቤተእስራኤላውያን ተስፋይቱ አገር አጓጉዛ ያጠናቀቀችው በ1983 ዓ.ም በግንቦት 17 እና 18 ቀናት ውስጥ በነበሩት ሠላሳ ስድስት ሰአታት ብቻ ነበር፡፡ ከ“ዘመቻ ሶሎሞን” አስደናቂ የአፈፃፀም ገድሎች ውስጥ ዋነኛውም ይሄው አስገራሚ የማጓጓዝ ፍጥነትና እንከን አልባ ቅንጅት ነበር፡፡ እነኚያ በሺ የሚቆጠሩ ቤተእስራኤላውያን ተሳፍረውበት የነበረው ሄርኩለስ አውሮፕላን ቴልአቪቭ ከተማ ቤን ጉርየን አውሮፕላን ማረፊያ እንደደረሠና እግራቸው ገና መሬት እንደረገጠ፣ እንዲህ ነው ተብሎ ሊገለጽ በማይቻል የደስታ ስሜት ተውጠውና በግንባራቸው ተደፍተው ቅድስቲቱን የተስፋዋን ሀገራቸውን እየተሳለሙ እንባቸውን አፈሰሱ፡፡ ከአስደናቂው የ“ዘመቻ ሶሎሞን” አሊያህ በኋላ ቀጣዩ ስራ የነበረው ቤተእስራኤላውያን ከእስራኤል ዘመናዊና አውሮፓዊ የአኗኗር ዘይቤ ጋር ተዋህደው እንዲኖሩ የማድረግ እንቅስቃሴ ነበር፡፡ ከዘመቻው በኋላ የነበሩት የመጀመሪያዎቹ አምስት አመታት ያለፉትም ይህን አድካሚና እልህ አስጨራሽ ስራ በማከናወን ነው፡፡ በእነዚህ አመታት ውስጥ በእስራኤል የሚኖሩ ቤተእስራኤላውያንን በተመለከተ ይዘገቡ የነበሩት አለም አቀፍ ዜናዎች ሁሉ ዋነኛ ትኩረታቸው ያደረጉት ስለ አስደናቂው የ“ዘመቻ ሶሎሞን” አፈፃፀምና ቤተ እስራኤላውያኑ በእርስ በርስ ጦርነት ከምትታመሠውና በማያቋርጥ የረሀብ አለንጋ ከምትገረፈው ኋላ ቀሯ ኢትዮጵያ ወጥተው ወደ ስልጡኗና ባለፀጋዋ ሀገር መግባት በመቻላቸው ምን ያህል እድለኛ እንደሆኑ ማሳየትና ማዳነቅን ነበር፡፡ ያኔ በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ሲሠጡ የነበሩ የእስራኤል ባለስልጣናት፣የሟቹን እስራኤላዊ ዊልያም ሳፋየርን የቆየ ንግግር ሳይጠቅሱ አያልፉም ነበር፡፡ 

      ዊልያም ሳፋየር በ1985 ዓ.ም በዘመቻ ሙሴ አማካኝነት ወደ እስራኤል የገቡትን ቤተእስራኤላውያን ካየ በኋላ፣ እስራኤላውያን እስከ ዛሬም ድረስ ታሪካዊና አይረሴ ነው የሚሉትን ንግግር አደረገ፡፡ “እነሆ አሁን በዚህ ታሪካዊ ዘመቻ አማካኝነት በሺ የሚቆጠሩ ጥቁር ህዝቦች በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በባርነት ተግዘውና በሠንሠለት ታስረው ሳይሆን በክብርና በዜግነት ወደ አንድ የሠለጠነ ሀገር ውስጥ መግባት ቻሉ!” ዊልያም ሳፋየር ረዥም ደቂቃዎች በፈጀው በዚያ ንግግሩ፣ የተስፋዋንና የቃልኪዳኗን መሬት እስራኤልን አምላክ እንደገባልን ቃል ኪዳን መሠረት ልንወርሳትና የዘላአለም ርስታችን ልናደርጋት እነሆ ሀገርና ባህር አቋርጠን መጣን የሚሉትን ቤተእስራኤላውያን በተደጋጋሚ የገለፃቸው፣ “ጥቁር ህዝቦች” እያለ እንጂ “ይሁዲዎች” ወይም “እስራኤላውያን” በሚል አልነበረም፡፡ ያኔ ከእስራኤላውያንም ሆነ ከቤተእስራኤል ተወካዮች የቀረበ ማስተካከያም ሆነ የተቃውሞ ጉምጉምታ ጨርሶ አልነበረም፡፡ ኢራናውያን “በደልን በማሸነፍ ለመበቀል መርሳትን የመሠለን ፍቱን ዘዴ የሚያስንቅ የለም” ይላሉ፡፡ የአረብ ቤዶይኖች በበኩላቸው ደግሞ “ያለ ሀይልና ስልጣን ንዴት ብቻውን አጥፊ ጠላት ነው” የሚሉት አባባል አላቸው፡፡ ቤተእስራኤላውያን የዊልያም ሳፋየርን ንግግር በዝምታ ያለፉት ከሁለቱ አባባሎች አንደኛውን አሊያም ሁለቱን በማሰብ፣ ምናልባትም ደግሞ የንግግሩ ዋነኛ መልዕክት በጊዜው በቅጡ አልገባቸው ኖሮ እንደሁ ያኔም ሆነ ዛሬ በትክክል የሚያውቅ የለም፡፡ በዚህም ተባለ በዚያ ግን የያኔው የዊልያም ሳፋየር ንግግር በተለያዩ የእስራኤል ባለስልጣናት በተለያየ ጊዜ መጠቀሱ፣ቤተእስራኤላውያኑ በወደፊቱ የእስራኤል ኑሮዋቸው ዘራቸውንና ቀለማቸውን በተመለከተ ምን አይነት ሁኔታ ሊያጋጥማቸው እንደሚችል ሁነኛ አመላካች ነበር፡፡ 

      “ዘመቻ ሶሎሞን” በድል ከተጠናቀቀ በኋላ፣ ባለፉት ሃያ አንድ አመታት ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ በተለይም ሃይማኖታቸውን ወደ ኦርቶዶክስ ክርስትና በመለወጣቸው የተነሳ “ፈላሻ ሙራ” እየተባሉ ተለይተው የሚጠሩ ቤተእስራኤላውያን እየተንጠባጠቡም ቢሆን አሊያቸውን በመፈፀም ወደ እስራኤል መግባት ችለዋል፡፡ ባለፈው አመት ሀምሌ ላይ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ የቀሩት “ፈላሻ ሙራ” ቤተእስራኤላውያን አሊያቸውን ፈጽመው ወደ እስራኤል እንዳይገቡ ሠበብ አስባብ እየፈጠረ ነገር ይጐትታል፣ ይባስ ብሎም ይከለክላል እየተባለ የሚወቀሰው የእስራኤል መንግስት፤ ሁሉም ቤተእስራኤላውያን ተጠቃለው ወደ እስራኤል እንዲገቡ ውሳኔ አስተላለፈ፡፡ አስፈፃሚው አካልም ቀደም ብለው እንደተካሄዱት አሊያዎች ሁሉ ይሄንንም ትዕዛዝ ለማስፈፀምም “ዘመቻ የእርግብ ክንፎች” የተባለ የጉዞ ዘመቻ በመንደፍ፣ የሁለት ዙር የጉዞ ፕሮግራም አዘጋጀ፡፡ በመጀመሪያው ዙር ሁለት መቶ አርባ፣ በሁለተኛው ዙር ደግሞ ሶስት መቶ ስልሳ በድምሩ ስድስት መቶ “ፈላሻ ሙራ” ቤተእስራኤላውያንን ባለፈው ጥቅምት ወር አጋማሽ ላይ በማጓጓዝ ለእስራኤል መሬት እንዲበቁ ተደረገ፡፡ ሶስት መቶ ስልሳዎቹን ቤተእስራኤላውያን የጫነው አውሮፕላን ቴልአቪቭ ቤን ጉርየን አውሮፕላን ማረፊያ እንዳረፈ፣ የተለያዩ የእራስኤል ባለስልጣናት በተገኙበት በተካሄደ ልዩ ስነስርአት፣ የኢትዮጵያ ቤተእስራኤላውያን ተጠቃለው ወደ እስራኤል እንደገቡና አሊያህአቸው እንደተፈፀመ በይፋ ተገለፀ፡፡ ቤተእስራኤላውያኑም ከአውሮፕላኑ እንደወረዱ የቀደሙት ወገኖቻቸው እንዳደረጉት ሁሉ፣ በከፍተኛ የደስታ ሲቃ ተይዘው መሬቲቱን እየተሳለሙ አነቡ፡፡ አንዳንዶቹም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ተንሰቅስቀው አለቀሱ፡፡ እነሱ እንዲህ ሲሆኑ እንዲሰፍሩበት የተወሰነው አቪም የመጠለያ ማዕከል የሚገኝበት የሻአር ሀነጌቭ ክልል ምክር ቤት አባልና የአይሁድ ድርጅት ለእስራኤል ሊቀመንበር በየተራ ንግግር እያደረጉ ነበር፡፡ በተለይ የአይሁድ ድርጅት ለእስራኤል ሊቀመንበር የሆኑት ናታን ሻረንስኪ “ከሀያ አመታት በኋላ በዚች በዛሬዋ እለት ወንድምና እህት ሲገናኙ ማየት በእውነት ተአምር ነው፡፡ 

      ኢትዮጵያውያን አይሁዶች እስራኤልን እንደለቀቁ የሀኑካህ (የሶሎሞን ቤተመቅደስ እንደገና መገንባትን ለመዘከር የሚደረግ) ክብረ በአል አልነበረም፡፡ አሁን ግን የሀኑካህን ብቻ ሳይሆን ሌሎቹንም ክብረ በአሎች አብረን እናከብራለን፡፡ ምስጋና ለእስራኤል መንግስት ይሁንና አሁን ሁላችንም እኩል አይሁዳውያን እኩል እስራኤላውያን ሆነናል” በማለት በከፍተኛ ጭብጨባ የታገዘ ንግግራቸዉን አደረጉ፡፡ በዚህ የናታን ሻረንስኪ ስሜታዊ ንግግር መካከል ግን በጭብጨባው ውስጥ የተዋጠ አንድ ከፍተኛ ማጉረምረም ነበር፡፡ ምንጩም በስፍራው ከተገኙት የቤተእስራኤሎች ድርጅቶች መሪዎችና የመብት ተሟጋች ተቋማት አመራሮች ነበር፡፡ የናታን ሻረንስኪ ንግግር ዊልያም ሳፋየር ከዛሬ ሀያ ሠባት አመት በፊት ካደረጉት ንግግር በእጅጉ ይለያል፡፡ ይሁን እንጂ አሁን የቤተ እስራኤላውያኑ ድርጅቶች መሪዎችና የመብት ተሟጋቾች የሰሙት ንግግር ካንጀታቸው ጠብ ሊልላቸው ጨርሶ አልቻለም፡፡ ለምን ቢባል እግራቸው የእስራኤልን መሬት ከረገጠበት ጊዜ አንስቶ፣ በዘራቸውና በቀለማቸው የተነሳ በየእለቱ የሚደርስባቸው መድልዎና ከፍተኛ የመብት ረገጣ የናታን ሻረንስኪን “ሁላችንም እኩል እስራኤላውያን ነን” ንግግር አምኖ ለመቀበል ጨርሶ የማይቻል ስላደረገባቸው ነበር፡፡ እስራኤል እንደ ሀገር ቆማ የዛሬውን ማንነቷን ያገኘችው፣ እንደቤተእስራኤሎቹ ሁሉ ከመላው ክፍለ አለማት በተሠባሠቡ አይሁዳውያን ህዝቦች መሆኑን ማስረዳት ያዋጁን በጆሮ እንደመናገር ተደርጐ ሊቆጠርብን ይችላል፡፡ ህንዳውያን “ቁመና፣ አለባበስና የፊት ለፊት ገጽታ አሳሳች ወይም አታላይ ነው” የሚል የዘወትር አባባል አላቸው፡፡ ቤተ እስራኤላውያን የእስራኤል ቁመናና የፊት ለፊት ገጽታ ለማመን በሚያስቸግር ሁኔታ አታላይና አሳሳች መሆኑን ለመረዳት የፈጀባቸው ጊዜ በአመታት የሚቆጠር ሳይሆን የአንድ እጅ ጣቶች እንኳን በማይሞሉ ወራቶች ብቻ ነው፡፡ ቤተ እስራኤላውያን የዘመናዊቷና የተስፋዋ ሀገራቸው የእስራኤል ኑሮ እንዳሰቡትና ለዘመናት ተስፋ አድርገው እንደጓጉለት እንዳልሆነ መረዳት የጀመሩትና በዘርና ቀለማቸው የተነሳ “ኩሽም” (ባሪያ) የሚል አዲስ ተቀጽላ ስም ያተረፉት፣ በአዲስ መጤነት የሰፈሩበትን ካምፕና ካምፑም የሚገኝበትን የከተማውን ስም ገና በቅጡ እንኳ ለይተው ሳያውቁት ነበር፡፡ እንዲህም ሁሉ ሆኖ ከጠቅላላው የእስራኤል ህዝብ እንደ ቤተ እስራኤሎች ያለ ተጋፊ ያልሆነ፣ የሰጧቸውን በምስጋና የሚቀበሉና ታጋሽ ልበ ሰፊ የህብረተሠብ ክፍል በምድረ እስራኤል በመብራት ፈልጐ ማግኘት ጨርሶ አይቻልም፡፡ በየጊዜው የሚደርስባቸውን ያን ሁሉ የዘረኝነት ግፍና በደል ከቻለ እንዲያወስግድላቸው ካልሆነ ደግሞ እንዲያስታግስላቸው ላለፉት ሀያ አምስት አመታት ያለመታከት ለእስራኤል መንግስት ጥያቄአቸውን አቅርበዋል፡፡ ለዚህን ያህል አመት ጥያቄአቸው የቀረበለት የእስራኤል መንግስት ይሠጣቸው የነበረው መልስ ግን ሁለት አይነት ብቻ ነበር፡፡“ከኢትዮጵያ የችጋርና የሰቆቃ ኑሮ በገላገልናችሁ ደሞ የምን ውለታ ቢስ መሆን ነው? ይልቁንስ የእስራኤል መንግስት ላደረገላችሁ ነገር ሁሉ በጣም አመስግኑት!” የሚልና “መጥፎ አናጢ ሁሌም በመጋዙ ያመካኛል” የሚል፡፡ (መቸም የዚች አነጋገር ትርጉም ለኢትዮጵያዊ ትጠፋዋለች ማለት ዘበት ነው!)እንግዲህ ልብ አድርጉ፡፡ በእንዲህ አይነት ሁኔታ መፍትሄ ቢከለክላቸውም ቤተእስራኤላውያን ለእስራኤል መንግስት ያላቸው ከበሬታና አድናቆት ይህን ያህል ቀንሶ አያውቅም ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ይኖሩ በነበረበት ጊዜ ያደርጉት እንደነበረው ሁሉ ከአምላክ ቀጥሎ በምድር ላይ ያላቸው መተማመኛ መንግስት ብቻ ነበር፡፡ያን ሁሉ በደልና ግፍ ሲቀበሉ ቀድመው ለአመጽ ከመጠራራት ይልቅ በየቤታቸው እየተብሰለሰሉ የእስራኤል መንግስት የሚወስደውን እርምጃ በከፍተኛ ትዕግስት የሚጠባበቁትም በዚህ የተነሳ ነበር፡፡ በ1985 ዓ.ም እንዳደረጉት አይነት በእስራኤል እየደረሠባቸዉ ያለውን ከፍተኛ የመብት ረገጣና የዘርና ቀለም መድልዎ ወደ አደባባይ በመውጣት የሚቃወሙት መሸከም ከሚችሉት በላይ ሲሆንባቸው ብቻ ነው፡፡ ያኔ የእስራኤል ራቢኔት ወይም የሀይማኖት አባቶች ጉባኤ ለከፍተኛ ውርደትና መሸማቀቅ የዳረጋቸውን የ “ሂዱሽ ሀይሁድ ሚክቫህ (የመታደግ ጥምቀት) ሀይማኖታዊ ትዕዛዝ አንድ ወር የዘለቀ የስራ ማቆምና የረሀብ አድማ በመምታት ተቃውመው ትዕዛዙን ማሻር ችለዋል፡፡ ከዛን ጊዜ ጀምሮም ቤተ እስራእላውያን ላለፉት ሀያ ሠባት አመታት እጅግ ብዙ የመብት ረገጣና የዘርና ቀለም መድልኦ እየተጋፈጡ ኖረዋል፡፡ ቤተእስራኤላውያን በእስራኤል ጠቅላላ ማህበረሠብ ውስጥ የተመደበላቸው ደረጃና በተግባርም የተዘጋጀላቸው ቦታ ከሁሉም የመጨረሻ የሆነው ብቻ ነው፡፡ ቤተ እስራኤላውያን በዘራቸውና በቀለማቸው የተነሳ የተስፋዋና የቃልኪዳኗ ሀገር እያሉ በሚጠሯት እስራኤል መቀዳጀት የቻሉት “የክብር ስም” “ኩሽም” የሚለውን ብቻ ነው፡፡ ባሪያ ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ባሳለፉት የብዙ ዘመናት የነዋሪነት ታሪክ የተለያዩ ችግሮችን አሳልፈዋል፡፡ በማናቸውም የኢትዮጵያ የማህበረሠብ ክፍል ዘንድ ግን ኩሽም ወይም ባሪያ ተብለው ተንቀውና ተዋርደው ጨርሶ እንደማያውቁ ራሳቸው እማኝ ናቸው፡፡ 


       ከማንም ምንም ነገር ይደረግልኛል ብለው የማይጠብቁ ወይም የማይተማመኑ፣ ሳይደረግላቸው በቀረ ጊዜ ቀረብኝ ብለው ስለማያዝኑ ወይም ስለማይበሳጩ እነሱ የተባረኩ ናቸው፡፡ ቤተ እስራኤሎች ግን ለዚህ ጨርሶ አልታደሉም፡፡ ችግሮቻው አይነታቸውም ሆነ ፈርጃቸው ብዙ ስለሆነ ከመንግስት የሚጠብቁት የዚያኑ ያህል ብዙ ነው፡፡ በዚህ ሂደት መሀል ታዲያ ሁለት ነገሮችን በሚገባ ለመረዳት ችለዋል፡፡ ከሌሎች የሚለምኑ የማማረጥን ፀጋ እንደማያገኙና “ግመል መካ ደርሶ መምጣት ቢችልም ሀጂ እንደማይባል” እነዚህን እውነታዎች በእርግጥም በደንብ አውቀዋቸዋል፡፡ የእስራኤል መንግስት ከሌሎቹ ዜጐቹ እኩል እንደማይመለከታቸው፣ መርጦና ይሁነኝ ብሎ አበጅቶ ከሠጣቸው የመጨረሻው ደረጃ ወደ ላይ ከፍ እንደማያደርጋቸው አሁን በደንብ ተገንዝበውታል፡፡ ይህ በየእለቱ በግልጽ የሚታይ እውነታ የሚያስደገንጠውና የሚያሳቅቀው ሌሎችን እንጂ የእስራኤል መንግስት ቁብ የሚሠጠው ወይም ነገሬ ብሎ የሚወዘወዝበት ጉዳይ አይደለም፡፡ የስነ ምህዳር ባለሙያዎች “መጥፎ አለባበስ እንጂ መጥፎ የአየር ፀባይ ብሎ ነገር የለም” ይላሉ ይባላል፡፡ የእስራኤል መንግስት የቤተ እስራኤሎችን ችግርና የእለት ተዕለት ፈተና ለማስረዳት የሚሞክረውም ይህንን አባባል በመጥቀስ ነው፡፡ የቤተእስራኤሎች ችግር የእስራኤል የአየር ሁኔታ መጥፎ ሆኖባቸው ሳይሆን እነሱ ለአየር ሁኔታው የሚስማማ ልብስ መልበስ ስላቃታቸው ወይም መጥፎ አለባበስ ስለለበሱ ነው የሚል ነው፡፡ በእስራኤል ምድር ላይ ያለው እውነታ የሚያሳየው ግን የእስራኤል መንግስት ከሚለው በእጅጉ የተለየ ይልቁንም ተቃራኒ የሆነ ነው፡፡ ቤተእስራኤላውያን የመጨረሻውን ዝቅተኛ የህብረተሠብ ደረጃ እንደያዙ በዘርና ቀለማቸው እለት ተእለት የሚደርስባቸውን ከፍተኛ በደል ራሳቸው ብቻ እየተጋፈጡ እንዲኖሩ በግልጽ አፍ አውጥቶ ባይናገረውም በተግባራዊ እንቅስቃሴው ግን ይሁን ብሎ የወሰነ ይመስላል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቤተእስራኤላውያን ላይ እየደረሠ ያለው ግፍና ከፍተኛ በደል ደግሞ አሁን የያዙትን የመጨረሻ ዝቅተኛ ደረጃ እንደያዙ እንዲኖሩ ብቻ ሳይሆን ዘራቸው በተራዘመ ሂደት ተመናምኖ እንዲጠፋም የፈለገ ይመስላል፡፡ የመካከለኛው ምስራቅ አረቦች “ቀኑ በረዘመ ቁጥር ብርዱም እየጠነከረ ይሄዳል” ይላሉ፡፡ ቤተእስራኤላውያን በእስራኤል የሚያሳልፉት አስቸጋሪና ፈታኝ ቀናቶች በረዘሙ ቁጥር የችግርና የፍዳቸው አይነትና መጠንም የዚያኑ ያህል እየጠነከረባቸው ሄዷል፡፡ “ኩሽም” ወይም ባሪያ እየተባሉ መጠራታቸውና በመኖሪያ አካባቢያቸውም ሆነ በስራ ቦታቸው የሚቀበሉት የመብት ረገጣና የዘር መድልዎ ሳያንሳቸው፣ አሁን ደግሞ የዘራቸው መባዛት የተፈለገ አልሆነም፡፡ እናም ተረኛው የጥቃት ኢላማ ሆኖ የተመረጠው የቤተእስራኤል እናቶች ወላድ ማህፀን ነው፡፡ ይህ አስደንጋጭና አስፈሪ የዘረኝነት በደል ቤተእስራኤላውያን ከመጥበሻው ድስት ወደ ጋመው ምድጃ እንዲዘሉ አስገድዷቸዋል፡፡ በመኖሪያ አካባቢያቸው፣ በስራ ቦታቸው፣ በትምህርት ቤት፣ በህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማት፣ በትራንስፖርትና በጤና ተቋማት ወዘተ በየእለቱ የሚጋፈጡትን የመብት ረገጣ፣ የዘርና የቀለም መድልዎ ለመንግስት አቤት የሚሉትን አቤት እያሉ፣ የማይሉትን ደግሞ በየራሳቸው ቤተሠብና ልብ ውስጥ ቀብረው እየተብሰለሰሉ ኑሮአቸውን ይገፉታል፡፡ ላለፉት አስር አመታት በሺ የሚቆጠሩ ቤተእስራኤሎች፣ ቤትና ግቢያቸው በህፃናት ልጆቻቸው የቡረቃ ጩኸት አልደምቅ ማለቱ፤ የሳራና የርብቃ አምላክ በሽልም ያውጣሽ የምትባል ቤተእስራኤላዊት እናት፤ የአብርሀም አምላክ እንኳን ዘርህን አበዛልህ የሚባል ቤተእስራእላዊ አባት እንደ ብርቅ የመታየቱ ነገር ለማንም የልብን ገልጠው የማይናገሩት “የውሽማ ሞት” አይነት ሆኖባቸው ነበር፡፡ የእስራኤልን መሬት ከረገጠችበት ከዛሬ ስምንት አመት ጀምሮ ከባሏ ጋር የምታደርገውን የሚስትነት ወግ ሳታጓድል ማህፀኗ ዘር ማፍራት አለመቻሉ ሌላ ተጨማሪ የጭንቀት አበሳ እንደሆነባት እንደ እማዋይሽ አይነት በሺ የሚቆጠሩ ቤተእስራኤላዊ እናቶች አሉ፡፡ እነሱ ጭንቀታቸውን የሚከፍሉት ዘወትር በየማለዳው በየምኩራቡ ደጀ ሰላም እየተደፉ ሳራን በእርጅና እድሜዋ እንኳን አስቧት በልጅ ፀጋ የባረካት አምላክ እነርሱንም እንዲያስባቸው በመማለድ ነበር፡

      ባለፉት አስር አመታት የቤተእስራኤል እናቶች ማህፀን፣ ዘር የማፍራት ፀጋው በሀያ በመቶ መቀነሱ በይፋ ሲነገር፣ ፈረሶቻቸው ከተሠረቁ በኋላ ጋጣቸውን የዘጉት የመሠላቸው ቤተእስራኤላውያኑ ነገሩ “ከአምላካችን ቢሆን ነው” በሚል ፊታቸውን ወደ አምላካቸው ለልመና ከማዞር በቀር ሌላ ያደረጉት ነገር አልነበረም፡፡ ቤተእስራኤላውያኑን ተጥደውበት ከነበረው የጋለ የመጥበሻ ድስት ወደ ጋመው ምድጃ እንዲዘሉ ያደረጋቸው ግን ሲባ ሪውቨን የተባለች የሴቶች መብት ተቆርቋሪ ያዘጋጀችው ጥናትና ዘጋቢ ፊልም “ቫኩም” በተሰኘ ፕሮግራም በእስራኤል የትምህርት ማሠራጫ ቴሌቪዥን ላይ ቀርቦ፣ ለህዝብ ከታየና የማህፀናቸውን መንጠፍ ሚስጥር ይፋ ካደረገው በኋላ ነበር፡፡ ወላድ ማህፀናቸው ያነጠፈው ወደ እስራኤል ለመምጣት በመዘጋጀት ላይ እያሉ በአሜሪካ የጥምር ስርጭት ኮሚቴ (American Joint Distribution Committee) በሚመራው ክሊኒክ ውስጥ ምንነቱንና የሚያስከትለውን ውጤት ሳይነግሩዋቸው በማባበልም በማስገደድም የወጓቸው ዲፓ-ፕሮቬራ የተባለ (በአሁኑ ጊዜ በየትኛውም ሀገር ጥቅም ላይ እንደማይውል ይነገራል) የወሊድ መቆጣጠሪያ ነው፡፡ በክሊኒኩ ይሠሩ የነበሩ ነርሶችና ሌሎች ባለሙያዎች ይህን መድሃኒት እንዴት እንዲወጉ እንዳደረጓቸው ሲባ ሪውበን ያነጋገረቻቸው እንደ እማዋይሽ አይነት ሰላሳ አምስት የቤተእስራኤል “ወላድ የነበሩ” እናቶች በደንብ አድርገው ተርከውታል፡፡ የአይሁዶች የታናካህ ቅዱስ መጽሀፍ፤ አምላክ የሰው ልጆችን በራሱ አምሳያ ሙሉ፣ ረቂቅና፣ ህብር አድርጐ እንደፈጠራቸው ግልጽ አድርጐ ያስረዳል፡፡ የሰው ልጅ ፍጥረት እዚህ ጐደለው የማይባል ሙሉ ነው፡፡ የሰው ልጅ የፍጥረት አካላቶቹ አንዳቸው ከአንዳቸው ተነጥለው ለብቻቸው የማይቆሙና ሙሉ የማይሆኑ በመሆናቸው ህብር ናቸው፡፡ ሙሉና ህብር በመሆኑም የሰው ልጅ አምላክ መለኮታዊ ሀይሉን የገለፀበት ረቂቅ ፍጥረት ነው፡፡ አይሁዳውያን በመበተናቸው ዘመን በአለሙ ሁሉ ተሰደው ይኖሩ በነበረ ጊዜ፣ ቅድስቲቱ መሬት እየሩሻሌይም ትዝ ባለቻቸው ጊዜ “እየሩሻሌይም ሆይ! ብከዳሽ ቀኝ አይኔ ትክዳኝ! ብረሳሽ ቀኝ ክንዴ ትርሳኝ!” ይሉ የነበረው ቀኝ አይናችንና ቀኝ ክንዳችን ከድተውን በህይወት እንዳለን ስለማይቆጠር፣ መቼውንም ጊዜ ቢሆን አንረሳሽም አንከዳሽምም ለማለትና እግረመንገዳቸውንም የፍጥረታቸውን ሙሉነትና ህብር ለማመልከት ነበር፡፡አምላክ የሰውን ልጅ ሙሉ ረቂቅና ህብር አድርጐ፣ በራሱ አምሳያ ከፈጠረው በኋላ በዝቶና ተባዝቶ ምድሪቱን እንዲሞላት በማዘዝ የራሱን ዘር በማብዛት የሚገኘውን ድንቅና ረቂቅ ፀጋ እንዲያይና እንዲካፈል አድርጐታል፡፡ ይህ ዘርን የማብዛት ልዩና ድንቅ ፀጋ አምላክ ለሰው ልጆች ሁሉ ያዘዘው ትዕዛዝ ብቻ ሳይሆን የሠጠው ተስፋና ምርቃትም ነበር፡፡ አምላክ የአይሁዳውያን ቀደምት አባት የሆነውን አብርሀምን እርሱን ብቻ እንዲያመልከውና ሂድ ወዳለው ቦታ እንዲሄድ ሲነግረው የሰጠው ተስፋና የገባለት ቃል “ዘሩን እንደ ሰማይ ኮከብና እንደ ባህር አሸዋ እንደሚያበዛው” ነበር፡፡ ሚስቱን ሳራን በመበለትነት እድሜዋ የባረካትና የዘመናት የመካንነት ሀዘኗን የካሳት ማህፀኗን በመክፈትና በመባረክ ነበር፡፡እናም የአምላክ ብዙ ተባዙና ምድሪቱን ሙሏት የሚለው ትዕዛዙም ሆነ “ዘርህን አበዛዋለሁ፣ ማህፀንሽንም እከፍታለሁ” የሚሉት የተስፋ ቃል ኪዳኖቹ የሰው ልጅን እንደፈጠረበት አፈጣጠር ጥልቅና ረቂቅ ናቸው፡፡ 
          የአይሁዶች የታናካህ ቅዱስ መጽሀፍ፤ የሰው ልጆችን ፍጥረት በተመለከተ ሌላም ተጨማሪ ማብራሪያ አለው፡፡ ይሄው ቅዱስ መጽሀፍ በአምላክ አምሳያ የተፈጠሩትን የሰው ልጆች በዘራቸው፣ በቀለማቸውና በባለጠግነት መጠናቸው ወይም በሌላ በማናቸውም መንገድና ሁኔታ ልዩነት መፍጠርና በዚህም ልዩነት የተነሳ በእነርሱ ላይ በደል ማድረስ በአምላክ አምሳያ ላይ ልዩነት መፍጠርና በደል እንደመፈፀም ተደርጐ እንደሚቆጠር ያስረዳል፡፡ በዚህ ልዩነት የተነሳ የሰው ልጆችን ያጠፋ ገዥም ሆነ ምስኪን ነዳይ የአምላክን አምሳያ እንዳጠፋ ስለሚቆጠር፣ የሀጢያቱ ዋጋ የሆነውን ሞት ይቀበላል፡፡ ይህን የቅዱስ መጽሀፍ ገለፃና ማሳሠቢያ በጥሞና እንዲያስተውሉት ለራሳቸው ለእስራኤል አይሁዳውያን መልሶ መናገር፣ አምላክ በመለኮታዊ ስልጣኑ የሰጣቸው ዘርን የማብዛት ልዩና ድንቅ ፀጋቸው ለተነጠቀና የእናቶቻቸው ወላድ ማህፀን “ወገኔና ህዝቤ” በሚሏቸው አይሁዶች እጅ እንዲነጥፍ ለተደረገባቸው ቤተ እስራኤሎች ካሏቸው በጣም ጥቂት ምርጫዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ይህን በማለት ለማስተላለፍ የሞከሩት “እኛን ብትንቁንና ባትፈሩን እንኳን አምላክን እንኳ ፍሩ” የሚል ሀዘን ያታከተው መልዕክት ነው፡፡ለሌሎች ግን እንደመናፍቅ ሊያስቆጥራቸው ይችል ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የእስራኤል መንግስትም ሆነ የኢትዮጵያ ቤተእስራኤሎችን አሊያህ ለማስፈፀም ይሠሩ የነበሩ የእስራኤል መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ እንዲህ ያለ አቻየለሽና አስደንጋጭ የዘረኝነት ጥቃት፣ በቤተ እስራኤሎች ላይ በመፈፀም ከጀርባቸው ያሉትን ድልድዮች ያቃጥሏቸዋል ተብሎ በቀላሉ መገመትም የሚቻል ነገር አልነበረም፡፡ ይሁን እንጂ የእስራኤል መንግስትም ሆነ የእስራኤል የአይሁድ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የታሰበውን እንዳልታሠበ፣ የተገመተውንም ጨርሶ እንዳልተገመተ እንዳደረጉት ያስመሰከሩት የተግባር ምላሽ በመስጠት ነው፡፡ የእስራኤል የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም ሆነ ክሊኒኮችን ይመራ የነበረው የአሜሪካ ጥምር የስርጭት ኮሚቴ (American Joint Distribution Committee) የሲባ ሪውቨንን በምስልና በፊልም የተደገፈ የጥናት ውጤት እንዲሁ በደፈናው ሽምጥጥ አድርገው ከመካድ ውጪ በነገሩ እጃቸው እንደሌለበት በተጨባጭ ማስረጃ ማስተባበል አልቻሉም፡፡ ከዚህ ይልቅ በዚህ ድርጊታቸው ለወዳጅም ሆነ ለጠላታቸው በግልጽ ማረጋገጥ የቻሉት ዋንኛ ነገር፣ ለቅዱስ መጽሀፋቸው ትዕዛዛትና መመሪያዎች ቁብ እንደማይሰጡና ከጠቅላላው የእስራኤል ህብረተሠብ በአሳዛኝ ሁኔታ የመጨረሻውን ደረጃ ይዘው እድሜ ዘመናቸውን እንዲዳክሩ ለፈረዱባቸው የኢትዮጵያ ቤተእስራኤሎች የሚራራ አንጀት እንደሌላቸው ብቻ ነው፡፡ በእስራኤል የሚኖሩ ቤተእስራኤሎችን እስከ ቁርጭምጭሚታቸው ድረስ ያሠመጣቸው የዘረኝነት ውሀ በጣም የተበከለና ቆሻሻ ነው፡፡


      ቆሻሻ ውሀ ደግሞ ማርካት የሚችለው የእሳትን ጥም ብቻ ነው፡፡ ነገሬ ብለው ከጉዳይ አልጣፉትም እንጂ ይህንንም እውነት የእስራአል መንግስትና ሸሪኮቹ የሆኑት መንግስታዊ ያልሆኑ የአይሁድ ድርጅቶች ያጡታል ብሎ መገመት ጨርሶ አይቻልም፡፡ጥንታዊዎቹ ሮማውያን፤ ዲያቢሎስ ወደ ንጉሡ ዘንድ ለመድረስ የቤተ መንግስቱን ደረጃ የሚወጣጣው በንግስቲቱ ደንገጡር ቀሚስ ተከልሎ ነው የሚል አሪፍ አባባል ነበራቸው፡፡ከምኩራቡ ጽስት ጀርባ ላይ ቆሞ ሲያደባ የነበረው “ዘረኝነት” ወደ እስራኤል መሪ ቤተመንግስት ሠተት ብሎ የገባው ግን ባገልጋዮቹ ቀሚስ ተከልሎ ሳይሆን የራሳቸውን የመሪውን እጅ ዘና ብሎ ጨብጦ ነው፡፡ ይህ እንዴት ሆነ? ለመሆኑ ቤተ እስራኤሎች ዛሬ በእስራኤል ውስጥ ያሉበት ሁኔታ ትክክለኛው ስዕል ምን ይመስላል? በሌላ ጽሁፍ እንገናኝ፡፡
      


የእስራኤል “ኩሽሞች”

        የእስራኤል  “ኩሽሞች

      አሳ ሁልጊዜ በመረብ ብቻ አይጠመድም፡፡ የመኖሪያ ቤት ግዢ የብድር ፕሮግራሙ እንዲህ ያለ አሳዛኝ ውጤት በማስመዝገብ ሲከሸፍ፣ ብዙዎቹ ቤተእስራኤሎችና እነሱን ለመርዳት ተብለው የተቋቋሙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የእስራኤል መንግስት ቤተእስራእሎችን ለማዋሀድ በሚል የቀረፃቸውን ሌሎች ፕሮግራሞች የአፈፃፀማቸውን ጉዳይ መለስ ብሎ ለመገምገም አረፍ የሚልበት ታዛና የጥሞና ጊዜ ያገኛል ብለው ተስፋ አድርገው ነበር፡፡በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ የድሩዝ ማህበረሠብ አባላት ተለይተው ከሚታወቁበት ነገሮች አንዱ ለሚኖሩበት ሀገር መንግስት ያላቸው የማያወላውል ታማኝነት ነው፡፡ በድፍን የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ውስጥ በሀገሬ የሚኖሩ ድሩዞች የተቃውሞ ድምፃቸውን አሠሙብኝ ወይም ደግሞ በአመጽ ተነሱብኝ ብሎ ስሞታውን ያሠማም ሆነ የሚያሠማ መንግስት ለመድሀኒትም ቢሆን ተፈልጐ አይገኝም፡፡ በ1970ና 80ዎቹ የሊባኖስ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት የራሳቸውን ሚሊሻ በማቋቋም ነፍጥ አንስተው ውጊያ የገጠሙት ህልውናቸዉን አደጋ ላይ ከጣሉት ታጣቂ የሚሊሻ ቡድኖች ጋር እንጂ ከሊባኖስ መንግስት ወታደሮች ጋር አልነበረም፡፡ ቤተእስራኤሎችም በእስራኤል የሚኖሩ “ድሩዞች” አይነት ነበሩ፡፡
     እግራቸዉ የእስራኤልን መሬት ገና ከመርገጡ ጀምሮ የሂብሩ ጋዜጦች መብታቸውንና ነፃነታቸውን የሚጋፋ፣ ሠብአዊ ክብራቸዉንም የሚያንቋሽሽ አስከፊ የጥላቻ ዘመቻ ሲከፍቱባቸው፤ ያይጥ ምስክር ድንቢጥ እንዲሉ ጋዜጦችንም ተከትለው የተለያዩ የእስራኤል ተቋማት፣ የተለያዩ የእስራኤል የመንግስት ባለስልጣናት፣ የሀይማኖት መሪዎችና የማህበረሠብ አባላት ተዘርዝሮ የማያልቅ የዘረኝነት በደል ሲፈጽሙባቸው በእስራኤል መንግስት ላይ የነበራቸው ተስፋና እምነት እንደተጠበቀ ነበር፡፡ ቤተእስራኤሎቹ ለእስራኤል መንግስት የነበራቸውን ክብርና እምነት እንዲህ በቀላሉ እሰየው ብለው ለድርድር የሚያቀርቡት ጉዳይ ጨርሶ አልነበረም፡፡ የተስፋዋ ሀገራችን በሚሏት እስራኤል ይሆናል፤ ያጋጥመናልም ብለው ጨርሰው ባልገመቱት ሁኔታ ያ ሁሉ ግፍና በደል ወደው እስኪጠሉ ድረስ ሲፈራረቅባቸው የእስራኤል መንግስት በወቅቱ የሠጣቸዉ መልስ አልነበረም፡፡ በዘርና በቀለማቸው የተነሳም ኢትዮጵያ ውስጥ ይኖሩ በነበረበት ጊዜ እንኳ ማንም ብሏቸው ወይም ጠርቷቸው የማያውቀውን “ኩሽም” (ባሪያ) የሚል መዘባበቻ ሲሆኑ የእስራኤል መንግስት ግን ተፈልጐም እንኳ ሊገኝ አልቻለም ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ቤተእስራኤላውያን ከተጣዱበት የዘረኝነት መጥበሻ ላይ እንዳሉ በፀጥታ መገላበጥን እንጂ በሚያምኑትና በሚያከብሩት የእስራኤል መንግስት ላይ ልባቸውን ለማሻከርም ሆነ ፊታቸውን ለማጥቆር ጨርሶ አልሞከሩም፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ በዚያን ወቅት በእስራኤል መንግስት ላይ ይህን ለማድረግ የሚያስችል አንጀት አልነበራቸውም ነበር፡፡
     እንደ እስራኤል ድሩዞች ተደርገው መቆጠር ጀምረው የነበሩት ቤተእስራኤሎች ማንም ሊያደርጉት ይችላሉ ብሎ ባልገመተው ሁኔታ በእስራኤል መንግስት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በተቃውሞ አደባባይ በመውጣት የእየሩሳሌምንና የሌሎችም የእስራኤል ታላላቅ ከተሞች ለአንድ ወር በዘለቀ ጠንካራ የተቃውም ስብሠባና ሠልፍ ቀውጢ ያደረጉት ሀይማኖታቸውን በተመለከተ በከፍተኛ ሀፍረት ላይ የጣላቸውና በእጅጉ ያሸማቀቃቸው በደል ከደረሠባቸው በኋላ ነበር፡፡ ቤተእስራኤሎች ከዚህ በፊት በከፍተኛ ትዕግስትና ሆደ ሠፊነት ይዘዋቸው የነበሩት የተለያዩ ፈርጀ ብዙ ችግሮች ሁነኛ መፍትሄ እንዲያገኙ የእስራኤል መንግስትን ሳያሠልሱ መወትወት የጀመሩትና አልፎ አልፎም የተቃውሞ ድምፃቸውን ማሠማት የጀመሩትም ከዚህ ጊዜ በኋላ ነው፡፡ የእስራኤል መንግስት ግን የቤተእስራኤሎችን ችግር የተረዳው ገልብጦ በተቃራኒው ነበር፡፡ ለእስራኤል መንግስት የቤተእስራኤሎች ችግር እውነተኛ ችግር ሳይሆን እነሱን ለማዋሀድ በሚል የሚያደረግላቸው መጠነ ሠፊ እርዳታ ስለበዛባቸው ከመቅበጣቸው የተነሳ የመጣ ችግር አድርጐ ነበር፡፡ እናም በየጊዜው የሚያቀርቡትን የመፍትሄ አቤቱታ ለማዳመጥ የሚያስችል ጊዜውም ሆነ ልቦናና የመስሚያ ጆሮ አልነበረውም፡፡
     ይልቁንስ ነገሩ ሁሉ የምግብ ፍላጐት ከመብላት ጋር ይመጣና ይጨምራል እንደሚባለው ሆኖበት ነበር፡፡ እናም አንዱ ጥፋት በጊዜ የመታረም እድል ማግኘት ሳይችል በሌላኛው ላይ እየተደራረበ ሄዶ፣ ቤተእስራኤሎቹን ከተቀረው የእስራኤል ማህበረሠብ ጋር በሚገባ ለማዋሀድ በሚል በእስራኤል መንግስት ተደግሶ የነበረውን “የቅልቅሉን” ድግስ የተጠሩት እንግዶች ሊቀምሱት እንዳይችሉ አድርጐ በአሳዛኝ ሁኔታ እንጀራውን አሻገተው፣ ወጡን እጅ እጅ እንዲል አደረገው፡፡ የእስራኤል መንግስት ቤተእስራኤሎች የራሳቸውን ቤት መግዛት እንዲችሉ ለማበረታታት በሚል በሠጣቸው ብድር አማካኝነት እስከዛሬ አስር አመት ድረስ አስር ሺ አምስት መቶ የሚሆኑ ቤተእስራኤላውያን አብዛኞቹ ባለ አንድ መኝታ ቤት የሆኑ አፓርታማዎችን ወይም የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ለመግዛት ችለዋል፡፡ ከተቀሩት ውስጥ አብዛኞቹ በመንግስት የኪራይ ቤቶች ውስጥ ሲኖሩ፣ ከዛሬ አስር አመት ወዲህ ወደ እስራኤል የመጡት ደግሞ ዛሬም ድረስ በመጠለያ ጣቢያዎችና በተንቀሳቃሽ ቤቶች ውስጥ ይኖራሉ፡፡ ለቤተእስራኤሎች ተዘርግቶ የነበረው የመኖሪያ ቤት ግዢ የብድር ፕሮግራም እንደተገለፀው የተወሰኑትን የቤት ባለቤት ሊያደርጋቸው ቢችልም የሚፈለገውንና ቀድሞውኑ የታሠበለትን ውጤት ሳያመጣ እንደከሸፈ በእስራኤል ክኔሴት (ፓርላማ) ተመስክሮበታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከእስራኤል መንግስት ሌላ በተጠያቂነት ቀርቦ ቃሉን ሊሠጥ የሚችል ተጠያቂ አካል ሊኖር አይችልም፡፡ እንዴት ቢባል… የእስራኤል መንግስት ይህን የብድር ፕሮግራም የጀመርኩት ቤተእስራኤሎችን ለመርዳት በሚል “ቅን” መንፈስ ነው በማለት ሞቅ ያለ ፕሮፓጋንዳውን ቢለቅም ለፕሮግራሙ አፈፃፀም ሙሉ ቀልቡንና ልቡን ጨርሶ አልሠጠም ነበር፡፡ ፕሮግራሙን ለማስፈፀም የተጠቀመባቸው ስትራተጂዎች በሙሉ የተንጋደዱና አቅም ባላቸው ባለሙያዎች የተያዙና የተመሩ ጨርሶ አልነበሩም፡፡ የፕሮግራሙ ጠቅላላ አሠራርም የግብር ይውጣ ነበር፡፡
     ይህን የብድር ፕሮግራም አሠራር በትኩረት በመከታተል አፈፃፀሙን በደንብ መገምገም የቻሉ የማህበራዊ ኑሮ ጥናት ባለሙያዎች፤ የእስራኤል መንግስት ቀድሞውን ቢሆን የእስራኤል “ኩሽም” የሆኑትን ቤተእስራኤሎች ከተቀረው “ናሽም” (ነጭ) የእስራኤል ማህበረሠብ ተለይተው በአንድ አካባቢ ብቻ ተከማችተው እንዲኖሩ ለማድረግ እጅግ በረቀቀ መንገድ ነድፎ ያዘጋጀው ፕሮግራም ነው እያሉ በሰላ ትችት ሲያብጠለጥሉት ኖረዋል፡፡ ይህን የባለሙያዎች ትችት ትክክል ነውም አይደለምም ብሎ መከራከሩ አጨቃጫቂ ሊሆን ይችላል፡፡ የሆኖ ሆኖ ግን የእስራኤል መንግስት በፈለገው አይነት አላማ ቢያዘጋጅም የመጨረሻው ውጤቱ ግን ከቀረበው ትችት ጋር አንድ አይነት ነበር፡፡ የመኖሪያ ቤት ለመግዛት ብድር የወሰዱ ቤተእስራኤሎች አብዛኞቹ ስራ አጥ ነበሩ፡፡ ስራ አላቸው የሚባሉትም ቢሆን እጅግ ዝቅተኛ ክፍያ በሚያስገኙ የስራ መስኮች ላይ የተሰማሩ ነበሩ፡፡ እናም ከወሰዱት ብድር ላይ ትንሽ ጨምረው በተሻሉና መካከለኛ ገቢ አላቸው ወደሚባሉትና ሁሉም አይነት የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች በተሟሉባቸው አካባቢዎች ውስጥ ቤት ለመግዛት የሚችሉ አልነበሩም፡፡ ሁሉም በብድር ያገኙትን ገንዘብ ይዘው ያመሩት ርካሽ የመኖሪያ ቤቶች ወደሚሸጡባቸው፣ ምንም አይነት የመሠረተ ልማት አገልግሎቶች ባልተዘረጉባቸው ኋላቀርና ጭራሹኑ ወደተዘነጉት አካባቢዎች ነበር፡፡ ይህም ሁኔታ በድህነት የተቆራመዱ፣ በጨለማ የተዋጡና፣ ከሌላው የእስራኤል ህብረተሠብ በእጅጉ የተጉላሉ “የኩሽም ቤተእስራኤሎች” የመኖሪያ ጌቶዎች እንዲመሠረቱ ዋነኛ ምክንያት ለመሆን በቃ፡፡ የማታ ማታ አፍላ፣ ኪርያት ጋት፣ ኦር ይሁዳ፣ ኪርያት ማላኪህና የመሳሠሉት በተለያዩ የእስራኤል ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ሠፈሮች “ናሽም” እስራኤላውያን ዝር የማይሉባቸዉ ወይም ዝር ሊሉባቸው በጣም የሚፈሯቸው የቤተእስራኤሎች መኖሪያ ጌቶ ሠፈሮች በመሆን አለም አቀፍ እውቅናን ለመጐናፀፍ ቻሉ፡፡ አሳ ሁልጊዜ በመረብ ብቻ አይጠመድም፡፡ የመኖሪያ ቤት ግዢ የብድር ፕሮግራሙ እንዲህ ያለ አሳዛኝ ውጤት በማስመዝገብ ሲከሸፍ፣ ብዙዎቹ ቤተእስራኤሎችና እነሱን ለመርዳት ተብለው የተቋቋሙ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የእስራኤል መንግስት ቤተእስራእሎችን ለማዋሀድ በሚል የቀረፃቸውን ሌሎች ፕሮግራሞች የአፈፃፀማቸውን ጉዳይ መለስ ብሎ ለመገምገም አረፍ የሚልበት ታዛና የጥሞና ጊዜ ያገኛል ብለው ተስፋ አድርገው ነበር፡፡ ይህንን ተስፋ ያደረጉትም “አንዴ የተሸነፈ ሁለት ጊዜ ያፍራል” የሚለው እድሜ ጠገብ የማስተዋልና የብልሀት አነጋገር መቼም ቢሆን ለእስራኤል መንግስት አይጠፋውም ከሚል ግምታቸው በመነሳት ነበር፡፡ ቶማስ ሐንዴ የተባለ ደራሲ “Mr. Nicholas” በሚል ርዕስ በ1952 ዓ.ም ባሳተመው መጽሀፍ፤ አደጋን ለመጋፈጥ የማይፈልጉ ቦቅቧቃ ሰዎች፤ ምንም ቢያደርጉ ምን በአስደናቂ ነገሮች የተሞላ ህይወት ለመኖርና አስደናቂ ውጤቶችን ለመቀዳጀት ከቶውንም አይችሉም ይላል፡፡ ይህ የቶማስ ሒንዴ አባባል በቀላልና አጭር አገላለጽ ሲቀመጥ “ጀብዱ ለጀብደኞች፣ (Adventure is for fare adventurous) ማለት ነው፡፡ ከ1973 ዓ.ም የዬም ኪፑር ጦርነት ድል ማግስት ጀምሮ እስከአሁን ድረስ በወይዘሮ ጐልዳ ሜየርም ሆነ በቤንጃሚን ናታንያሁ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የተመራው የእስራኤል መንግስት ወታደራዊ የሆነውን ነገር ለጊዜው ትተን ማህበራዊ ጉዳዮችን ብቻ በተመለከተ የወሠዳቸውን የተለያዩ የፖሊሲም ሆነ ሌሎች እርምጃዎችን በስሱ በመገምገም ብቻ የእስራኤል መንግስት ጀብዱ (Adventure) አድናቂና ጀብደኛ (Adventurous) መንግስት እንደሆነ ለመገንዘብ ምንም አይነት የአዕምሮ ብሩህነትን አይጠይቅም፡፡
     አሳዛኙ ነገር ግን እነዚያ ቤተእስራኤሎችና የቤተእስራኤል ድርጅቶች ይህንን በወጉ መገንዘብ አለመቻላቸው አሊያም ጨርሰው መዘንጋታቸው ነበር፡፡ በዚህ የተነሳም የእስራኤል መንግስት፤ የመጀመሪያው ውሸት ወደ ሁለተኛው ውሸት ይመራል እንደሚባለው አይነት ከመጀመሪያው ስህተት ወደ ሁለተኛው ተሸጋገረ፡፡ የእስራኤል መንግስት ቤተእስራኤሎችን ለማዋሃድ በነደፈው ማስተር ፕላን፣ የስራ እድልን በተመለከተ ያስቀመጠው ዋነኛው ግቡ ለቤተእስራኤሎች የሙያና የክህሎት ስልጠና መስጠት የሚል ነው፡፡ በዚህ መሠረት የእስራኤል የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ለቤተእስራኤሎቹ በቂያቸው ነው ብሎ የመረጠላቸው የሙያና የክህሎት የስልጠና መስኮች የብረታብረት፣ የእንጨት ስራ፣ የነርሲንግ፣ የሆቴል መስተንግዶና፣ የልብስ ስፌት ናቸው፡፡ የእውነት ለመናገር ባለእጅነትን አምላክ ሁልጊዜ ለቤተእስራኤሎች ብሎ የጣፈው ሙያ ይመስላል፡፡ ይህ ላይ ላዩን ሲያዩት አሪፍ ነገር ይመስላል፡፡ ነገር ግን ቤተእስራኤሎች አስቀድሞ በተመረጠላቸውና በተወሰነባቸው በእነዚህ የስልጠና መስኮች የሙያ ስልጠና እንዲወስዱ ዝግጅት እየተደረገ ባለበት ወቅትም ሆነ ከዚያ ቀደም ብሎ እነዚህ የስራ መስኮች በፍልስጤማውያንና በሌሎች ዜጐች ከአፍ እስከደገፋቸው ተይዘው ነበር፡፡ እናም ቤተእስራኤሎቹ እንደታሰበው ሰልጥነው ቢወጡም፣ በእስራኤል የስራ እድል መድረክ ላይ ተወዳድረው ስራ ማግኘት በእጅጉ አዳጋች ሆነባቸው፡፡ በመጨረሻም ያተረፉት ነገር የእስራኤልን አውራጐዳናዎች ማጽዳት፣ መናኛ ስራዎችን እጅግ መናኛ በሆነ ክፍያ መስራትና የእስራኤል የአዲስ መጤዎችና የውህደት ሚኒስቴር የሁልጊዜም የእርዳታ ጥገኛ ሆኖ መቅረትን ነበር፡፡ በትምህርትና በሌሎች የማህበራዊ ዘርፎች የተገኘው ውጤትም ከዚህ ጨርሶ የተለየ አልነበረም፡፡ ቤተእስራኤላውያን በተሻለ ተዋህደውበታል ተብሎ ሊጠቀስ የሚችለው ተቋም ቢኖር የእስራኤል የጦር ሀይል ብቻ ነው፡፡
     ቤተእስራኤሎች እውነተኛ እስራኤላዊ መሆናቸውንና ለእስራኤል ያላቸውን ፍቅርና ታማኝነት የህይወት መስዋዕትነትም ቢሆን በመክፈል ለማሳየት ቁርጠኛ አላማ የያዘና ለዚህም የምራቸውን የተዘጋጁ ነበሩ፡፡ የእስራኤል የመከላከያ ሠራዊትን በገፍ የተቀላቀሉትም በዚህ የተነሳ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ተቋምም ቢሆን ያጋጠማቸው የዘረኝነት መድልዎ እንዲህ በቀላሉ ተነግሮ የሚያልቅ አይደለም፡፡ የእስራኤል መንግስት ችግሮቹን በጊዜ ለመፍታት ባለመቻሉ ሳይሆን ፈጽሞ ባለመፈለጉ የተነሳ በሁሉም ነገር የመጨረሻውን ዝቃጭ ደረጃ የያዘ አንድ የእስራኤል ማህበረሠብ ለመፍጠር ቻለ፡፡ ቤተእስራኤሎችም የማታ ማታ ከመላው የእስራኤል ማህበረሠብ ተለይተው የዘረኝነት ጥቃትና መድልዎ ሰለባ ሆነውና የመጨረሻውን ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ይዘው ራሳቸውን አገኙት፡፡ ይህም ሁኔታ የአብዛኞቹን ቤተእስራኤሎች ቤተሠብ ክፉኛ አመሠቃቀለው፡፡ በእድሜ የገፉት ለከፍተኛ ግራ መጋባት ሲዳረጉ፣ ወጣቶቹ ደግሞ በከፍተኛ የማንነት ቀውስ ውስጥ በመውደቃቸው “ራስታ” ለመሆን ባዘኑ፡፡ እነዚሁ ቤተእስራኤሎች በከፍተኛ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ ስለወደቁ፣ በወንጀል ድርጊት መሳተፍ፣ የወንጀል ቡድን አባል መሆን፣ አደንዛዥ እጽ መጠቀምና ማዘዋወር ድርጊት ውስጥ መሳተፍ ጀመሩ፡፡
     በዚህም የተነሳ የቤተእስራኤል ወጣቶች የእስራኤልን እስር ቤቶች ማጨናነቅ ተያያዙት፡፡ ለህይወት ጉጉት ማጣታቸውና ከህይወት ትግል ማፈግፈጋቸውም መገዳደልንና ራስን ማጥፋትን እንደ ዋነኛ የችግር መገላገያ መፍትሄ አድርገው ይቆጥሩት ጀመር፡፡ የተቀረው የእስራኤል ህዝብ በአባታቸው ኖህ እንደተባረኩት ልጆች እንደ ሴምና ያፌት ናቸው፡፡ ማርና ወተቱን እለት ተዕለት እየተቆጣጠረ የቆዳ ስልቻቸውን የሚሞላላቸው የራሳቸው አሳላፊ አላቸው፡፡ የቤተእስራኤሎች ኩባያ ግን ባዶ ነው፡፡ ምክንያቱም ከሀገሪቱ የማርና የወተት ሠልፍ የእነሱ ተራ ከሁሉም የመጨረሻው ስለሆነ ነው፡፡ አሁን እነሱ ለአምላካቸው እያቀረቡት ያለው ፀሎት አንድ ብቻ ነው፡፡ አምላካቸው የራሳቸውን ነህምያ (ነቢይ) እንዲሠጣቸው!! አሜን ያድርግላቸው!

ምንጭ፦ አዲስ አድማስ ጋዜጣ

"ጃ……. ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ"


                                         የእህተ ሙሴን እንጉርጉሮ


        መቼም ጆሮ የማይሰማው ነገር የለም ፤ እናንተዬ ፦ "ፈላሻነት" እንደ ስለት ልጅ ጣጣ የበዛው ሆነሳ !! ነጭ ወንድሞቻቸው ምነው ዘመቱባቸው እሳ ? መጽሐፉ እንዳለው " ወንድም በወንድሙ ላይ ይነሳል " የትንቢቱ ፍጻሜ በእነርሱ ሆኖ ነው ወይስ እኛ እናስብላቸው ፣ እኛ እንወስንላቸው ማለታቸው ነው ?
ወይ መሸወድ ፥ ለሀበሻ ልጅ ነጭ "አምላክ" እንጂ መች "ወንድም" ኖሮት ነው ወንድሞቻቸው የምንለው ። "ጃ……. ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ" አረ "ጃ" በለው !።
        ደግሞም "አምላክ ትሆናላችሁ" የተባሉት ለፈርኦንና ለሰራዊቱ እንጂ መች ለቀዳማዊ ምንሊክና ለዘሩ "ፈላሾች" መች ትሆናላችሁ አለ። በዚህ ላይ እኚህ "ፈላሾች" ፈልሰውበት የነበረው ቦታ የታላቁ ነብይ በሂብሩው ቋንቋ "ሙሼ ራቤኑ" ብለው የሚጠሩት የነብዩ ሙሴ ሚስት ሀገር፤ ንጉሳችን የሚሉት የንጉሥ ዳዊት ልጅ፣ የሰሎሞን ልጅ፣ የምንሊክ ሀገር ኢትዮጵያ ነው በክብር የተቀመጡበት። ይህንን ደግሞ እነርሱም ሆነ እነርሱ ያውቁታል። ይሄው "ጃ" ብለናል።
         ታዲያ እነዚህ "ጃ" ያልንላቸው ዘእምነገደ ይሁዳ የነጭ ይሁዳዊያን መጫወቻ ከሆኑ ዘመን ተቆጠረ ። ስንት ዘመን በኢትዮጵያ ጠብቀውት የነበረው እምነትና ስራታቸው እየተበረዘና ወደ ሌሎች እምነቶች እየተቀለበሰ ነው ። በዚህ ላይ አንዱ "ነጭ አማልእክት" ባሰኘው ጊዜ ይነሳና "እናንተ እውነተኛ ይሁዳዊያን አይደላችሁም፣ ተገረዙ፣ ልጅህና ልጄ አብረው ባንድ ክፍል አይማሩም  " ይላል ፤ ሌላው "ባለተራ አምላክ" ደግሞ  "ደምህን ደፋነው፤ እኔ በምዝናናበት ናይት ክለብ አትደረስ፣እኔም በምነዳው አውቶብስ አትሳፈር   "ይላል። ስንቱ ተዘርዝሮ ያልቃል።
         የዘንድሮው ደግሞ ሌላ ጉድ ነው። ምን ነበር የሚባለው "ጉድ ሳይሰማ  "መስከረም………. ቢጠባም ከፈላሾች መንደር የጉድ ዶፍ አላባራም።በጎንደር የሚገኙ ወደ እስራኤል ሀገራቸው ለመምጣት በመጠባበቅ ላይ ያሉ "ፈላሾች" የእርግዝና መከላከያ ካልወሰዳችሁ ወደ እስራኤል አትገቡም ሲባሉ ያለውድ በግዳቸው ወደ ሆዳቸው አንከባለሉት። ይህም ሳይበቃ እስራኤል ከመጡ በኋላ እንኳን ሳይቀር እንክብሎቹን እንዲወስዱ እየተገደዱ ነው።
       እነዚህ ወገኖቻችን በጎንደርና በአዲስ አበባ ከመንደራቸው ርቀው መጉላላታቸው መሰቃየታቸው ሳያንስ "ፍሬህን ወልደህ ለመሳም ኢሹር (ፍቃድ) ካልሰጠንህ ልትወልድ አትችልም" እያሉት ነው። የሚገርመው ነገር ከዛሬ ስልሳ ዓመት በፊት ጀምሮ  እነርሱ ከየነበሩበት ሀገር ወደ ተቀደሰችው ከነአን ሲገቡ ያለምንም ኢሹር ነበር፤ የእኛዎቹ "ፈላሾች"  ግን እስራኤል ለመድረስ የስንትና ስንት መስሪያ ቤት ቢሮና የባለስልጣን ኢሹር ያስፈልጋቸዋል። አረ ጎበዝ "ጃ" በል።
         ምድሪቱ እኮ የቃል ኪዳን ሀገርነቷ ለሁሉም የሀይሁድ ዘር ነው። እነርሱም የአብርሃም፣የይስሐቅ፣የያዕቆብ ልጆች ፤እነዚህም እንደዛው  ልጆች። ወይስ የእህተ ሙሴን እንጉርጉሮ ዛሬም ማዜም ፈልገው ነው። "ጃ" ብለናል "ሞአ ፈላሻ፣ ዘእምነገደ ይሁዳ"


“ጥሩ ኢትዮጵያዊ ማለት የሞተ ኢትዮጵያዊ ብቻ ነው--”

                                 የቤተእስራኤላውያኑ ምሬት በተስፋይቱ አገር 
 
     በተለያዩ ህብረ ቀለማት ያሸበረቁ ላባዎች ለአይን ማራኪ የሆኑ ወፎችን ይፈጥራሉ፡ ቤተእስራኤላውያን በኢትዮጵያ ያሳለፉት ከእጅ ወደ አፍ የሆነ የድህነት ህይወት እንደ ነበር መናገር ቀባሪውን እንደማርዳት ይቆጠራል፡፡ እናም ማራኪ ወፍ ለመሆን የሚያስችል ጌጠኛ ላባ አልነበራቸውም፡፡
በዘመቻ ሙሴም ሆነ በዘመቻ ሰሎሞን ወቅት የመዘጋጃ ጊዜአቸውን ያሳለፉት ዘመቻውን ያስተባብሩ የነበሩ የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ የአይሁድ ድርጅቶች ይሠጧቸው በነበረው የምግብ፣ የመጠለያ፣ የአልባሳትና፣ የጤና እርዳታ ነበር፡፡ በልባቸው ለዘመናት አትመው ይዘዋት የነበረው የተስፋዋ ሀገራቸው እስራኤል የተቀደሰችም ነበረችና ወደ እስራእል ለመግባት ያደረጉትን የመጨረሻ ዝግጅት ያጠናቀቁት በቻሉት መጠን ራሳቸውን በማዘጋጀት ነበር፡፡

    እጃቸው እርጥብ የነበሩት ለራሳቸውና ለልጆቻቸው አዳዲስ ልብሶችን በመግዛት፣እጅ ያጠራቸው ደግሞ የነበሯቸውንና የአይሁድ ድርጅቶቹ የሠጧቸውን ልብሶች አጥበው ለብሠው ነበር፡፡ የረጅም ዘመናት የድህነት ህይወት የራሱን ወፍራም አሻራ ያተመበትን ወዙ የተመጠጠ ጐስቋላና የገረጣ ፊታቸውንም ባገኙት አንባሬ ጭቃ ቅባት በማውዛት፣ በእነሱ አቅምና ችሎታ መጠን ወደ ቅድስቲቱ ሀገር አምረውና ደምቀው ለመግባት በእጅጉ ተጣጥረው ነበር፡፡
ይህ ሁሉ መሽሞንሞናቸው ግን የእስራኤላውያኑን ቀልብ ሊስቡና በአይናቸውም ዘንድ ሞገስን ሊያስገኝላቸው ሳይችል ቀረ፡፡ ገና ወደ እስራኤል እንደገቡ እስራኤላውያኑ እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት አቅፈው ቢስሟቸውም ከኢትዮጵያ ስለሚመዘዘው ዘርና ቀለማቸው፣ ስለ አዳፋ ልብሳቸው፣ ስለተጐሳቆለውና ስለገረጣው ሰውነታቸው ካይናቸው ይልቅ ልባቸው አብዝቶ ተጠይፏቸው ነበር፡፡
     በድፍን የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት እጅግ የሠለጠነና በስነምግባር የታነፀ ነው እየተባለ ዝናው ይናኝለት የነበረው የእስራኤል የሂብሩ ቋንቋ ፕሬስም፣ የአዲስ መጤዎቹን ባይተዋር ቤተእስራኤላውያን ነፃነትና ሰብአዊ መብት የሚጋፋ ሰብአዊ ክብራቸውንም ክፉኛ የሚያንቋሽሽና የሚያዋርድ ከፍተኛ ዘመቻ በመክፈት፣የእስራኤላውያኑን ዘረኝነትና ገና በማለዳው በቤተእስራኤሎች ላይ የያዙትን የልባቸውን መጠየፍ አለአንዳች ይሉኝታ ይፋ አደረገው፡፡ በየትኛውም ሀገርና የመንግስት ስርአት ውስጥ ቢሆን ፕሬስ እሳት ነው፡፡ እሳት መልካም አገልጋይ መጥፎ አለቃም ነው፡፡
በአግባቡ የተያዘ እሳት የሚሠጠውን ግልጋሎትና ከቁጥጥር ውጭ የሆነው ደግሞ የሚያደርሰውን ጥፋት ማንም ቢሆን በቀላሉ መረዳት ይችላል፡፡ የእስራኤል ፕሬስም በቤተእስራኤላውያኑ ላይ ከፍቶ የለቀቀባቸዉ ከቁጥጥር ውጪ የሆነ እሳትን ነበር፡፡
ቤተእስራኤላውያኑ ገና ወደ እስራኤል ከመግባታቸው እስራኤላውያኑ በዘር ጥላቻ ተመርዘው ያቀረቡላቸዉ ምግብ ጠንቀኛ መድሀኒት ቢሆንባቸውና አለመጠን ግራ ቢያጋባቸውም መርሳት ክፋትን ለመበቀል ምርጡ ዘዴ መሆኑን መገንዘብ በመቻላቸው፣ሁሉን ነገር ለመርሳት ሞክረው ነበር፡፡
በላይ በላዩ እንደ ጋራ ላይ ናዳ የወረደባቸው የዘረኝነት ጥቃት ግን ለመርሳትም እንኳ እድል ሳይሠጣቸው ቀረ፡፡ የእስራኤል የደም ባንክና የአምቡላንስ አገልግሎት ድርጅት የሆነው “ማገን ዴቪድ አዶም” ያለ አንዳች ተጨባጭ ማስረጃ እንዲሁ በግምት ብቻ ቤተእስራኤላውያኑ የለገሱትን ደም በኤችአይቪ/ኤድስ ቫይረስ የተበከለ ነው በሚል እየደፋ ሲያቃጥል መኖሩን ይፋ አደረገ፡፡ እንደ ማሻ ሐሮሽና እና ሪሾን ላዚወን የመሳሠሉ የከተማ ማዘጋጃ ቤቶች ቤተእስራኤላውያን ወደ ከተሞቻቸው መጥተው እንዲሰፍሩና እንዲኖሩ ጨርሶ እንደማይፈልጉ በግልጽ አሳወቁ፡፡
        ከእስራኤል የኦርቶዶክስ አይሁዶች ጠንካራ ሀይማኖታዊ ቡድኖች ውስጥ አንዱ የሆነው “ሐባድ” የቤተእስራኤላውያንን አይሁድነት እንደማይቀበል በመግለጽ፣የቤተእስራኤላውያን ልጆች ቡድኑ አቋቁሞ በሚያስተዳድራቸው የመዋዕለ ህፃናት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ገብተው መማር ጨርሶ እንደማይችሉ በጥብቅ አስገነዘበ፡፡ ፔታህ ቲክቫህ በተሰኘ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የኒር ኤዚዎን ትምህርት ቤትም፣ ቤተእስራኤላውያን ተማሪዎች በትምህርት አቀባበላቸው ሰነፎች ስለሆኑና ሌሎች እስራኤላዊ ተማሪዎችን ስለሚጐትቱ አንድ ላይ መማር አይገባቸውም በሚል ቤተእስራኤላዊ ተማሪዎችን ለይቶ በመልቀም በአንድ ክፍል ውስጥ ማጐሩን ትንሽም እንኳ ቅር ሳይለው በይፋ ማሳወቅ ቻለ፡፡ የእስራኤል ባንኮች፣ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ የአየር ማረፊያዎች ባለስልጣን፣ የመብራት ሀይል ኮርፖሬሽን ወዘተ ደግም በተራቸው ቤተእስራኤላውያንን ሠራተኞቻቸው አድርገው ለመቅጠር ምንም አይነት ፍላጐት እንደሌላቸው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ አቋማቸውን ግልጽ አደረጉ፡፡ በርካታ ቤተእስራኤላውያን ከሚኖሩባቸው የእስራኤል ከተሞች ውስጥ በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀሰው ከተማ ኪርያት ማላኪህ ናት፡፡ ይህችን ከተማ እስራኤላውያን ቤተእስራኤሎችን በሚገባ ያዋሀድንባት ሞዴል ከተማችን እያሉ ነጋ ጠባ ያሞካሹዋታል፡፡ ነገር ግን ከየትኞቹም ከተሞች በላቀ ሁኔታ በቤተእስራኤላውያን ላይ አይን ያወጣ የዘረኝነት ጥቃት የሚካሄደው በዚች ከተማ ውስጥ ነው፡፡ በዚች ከተማ ውስጥ ከሚካሄዱት የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ (ሪል ኢስቴት) ፕሮጀክቶች ውስጥ የአንዱ ፕሮጀክት ኮንትራክተር የሆነው ያዕቆብ ቫክኒን የሚገነባቸውን የመኖሪያ ቤቶች እንቅ ቢል እንኳ ለቤተእስራኤላውያን ሊሸጥላቸው እንደማይፈልግ ያለ አንዳች ማመንታት አሳወቀ፡፡
        “ዓሩጽ 2 (Channel-2)” የተሠኘው የእስራኤል ቴሌቪዥን ደግሞ በኪርያት ማላኪህ ከተማ ምክር ቤት ውስጥ የባር ይሁዳ ሠፈር ነዋሪዎች፣ለቤተእስራኤላውያን ቤት ለማከራየትና ላለመሸጥ እየተማማሉ ሲፈራረሙ በማሳየት ተመልካቹን ሁሉ አስገረመ፡፡ይሄው ቴሌቪዥን ይህን ድርጊት ብቻ ማሠራጨቱ ስላልበቃው፣ ይግረማችሁ ብሎ የዚሁ የባር ይሁዳ ሠፈር ነዋሪዎች የሆኑ ሁለት እስራኤላውያን በየተራ ቀርበው “ጥሩ ኢትዮጵያዊ ማለት የሞተ ኢትዮጵያዊ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ልክ እንደ አቶሚክ ቦንብ ይሸታሉ፡፡” በማለት ነውርንም ህግንም ሳይፈሩ የተናገሩትን የለየለት ዘረኛ ንግግር በተጨማሪ በማሠራጨት ማን አለብኝነቱን በሚገባ ለማስመስከር ቻለ፡፡ አሁን በቅርቡ የተጋለጠው ድርጊት ደግሞ የቤተእስራኤላውያን የወሊድ መጠን ባለፉት አስር አመታት ጊዜ ውስጥ በሀያ በመቶ የቀነሰበትን ሚስጥር የፈታና ቤተእስራኤላዊ እናቶች ላለፉት አስር አመታት ግቢያቸው የህፃናት የቡረቃ ድምጽ እርቆትና የሳራና የርብቃ አምላክ በሽልም ያውጣሽ ተብለው ሳይመረቁ፣ ማን ምን አድርጓቸው ወላድ ማህፀናቸው እንደነጠፈ የሚያስረዳው አሳዛኝ የዘረኝነት ገድል ነው፡፡
    እንግዲህ ልብ አድርጉ፡፡ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩት ታሪኮች በቤተእስራኤላውያኑ ላይ የተፈፀሙትን የዘረኝነት ጥቃቶች ላይ ላዩን ለማመልከት ለናሙና ያህል ብቻ የቀረቡ ታሪኮች ናቸው፡፡ቤተእስራኤላውያን ተቆጥረውና ተዘርዝረው የማያልቁ እነዚህን መሰል የዘረኝነት ጥቃቶችን ላለፉት ሀያ ሠባት አመታት ወደው እስኪጠሉ ድረስ ሲቀበሉ ኖረዋል፡፡ በአይሁድ እምነት ዘንድ ለምዕመናኑ እንደ ዋና ዋና ፀጋዎች ተደርገው ከሚቆጠሩት መልካም ድርጊቶች ውስጥ አንዱ መልካም የእንግዳ አቀባበል ነው፡፡ የአይሁዶች የታናካህ ቅዱስ መጽሀፍ፣ ሰዎች ሳያውቁት የአምላክ ቅዱስ መላዕክት በእንግድነት ሊመጡባቸው ስለሚችሉ ለማናቸውም አይነት እንግዶች መልካም አቀባበልና መስተንግዶ በማድረግ፣የአምላክን ምርቃትና በረከት እንዲያገኙ የቀደመውን አባታቸውን አብርሀምን በምሳሌነት በመጥቀስ፣ የእርሱን አብነት እንዲከተሉ ያሳስባል፡፡ በዘፍጥረት 18 እንደተገለፀው፣ አብርሀም በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ ሶስት ሰዎች በፊቱ ቆመው ባያቸው ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነስቶ ሮጠ፡፡ ወደ ምድርም ሠገደና ከዛፏ በታች እንዲያርፉ፣እግራቸውንም እንዲታጠቡና በቁራሽ እንጀራም ልባቸውን እንዲደግፉ ተማፀናቸው፡፡ ፈቃደኝነታቸውን እንዳገኘም በመልካም ሁኔታ አስተናገዳቸው፡፡ በአብርሀም መልካም መስተንግዶ ልባቸው ደስ የተሰኙ እንግዶችም በልጅ ፀጋ ያልታደለው የባለቤቱ የሳራ ማህፀን እንደሚለመልምና ልጅንም እንደምታገኝ አብስረውት ሄዱ፡፡እነዚያ ሶስት እንግዶች የአምላክ መልዕክተኞች ነበሩና የነገሩት ብስራት አምላክ ለሠራው መልካም ስራ አምላክ የሰጠው ምርቃት ነበርና አብርሀም በኋላ የእስራኤላውያን አባት የሆነውን ይስሀቅን ማግኘት ቻለ፡፡ እስራኤላውያን በቤተእስራኤላውያን ላይ የዘረኝነት ጥቃት በመፈፀም ያጡትና የተላለፉት ይህንን የመልካምነትን ፀጋና ከመልካም ስራ የሚገኝን የአምላክን በረከት ነው፡፡ ነገሮች ሁሉ በዚህ ብቻ ቢያልፉ ኖሮ ግን ለሁሉም ወገን ጽድቅ በሆነ ነበር፡፡ (ይቀጥላል)

 ምንጭ ፦ አዲስ አድማስ ጋዜጣ