Saturday, February 16, 2013

"ጃ……. ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ"


                                         የእህተ ሙሴን እንጉርጉሮ


        መቼም ጆሮ የማይሰማው ነገር የለም ፤ እናንተዬ ፦ "ፈላሻነት" እንደ ስለት ልጅ ጣጣ የበዛው ሆነሳ !! ነጭ ወንድሞቻቸው ምነው ዘመቱባቸው እሳ ? መጽሐፉ እንዳለው " ወንድም በወንድሙ ላይ ይነሳል " የትንቢቱ ፍጻሜ በእነርሱ ሆኖ ነው ወይስ እኛ እናስብላቸው ፣ እኛ እንወስንላቸው ማለታቸው ነው ?
ወይ መሸወድ ፥ ለሀበሻ ልጅ ነጭ "አምላክ" እንጂ መች "ወንድም" ኖሮት ነው ወንድሞቻቸው የምንለው ። "ጃ……. ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ" አረ "ጃ" በለው !።
        ደግሞም "አምላክ ትሆናላችሁ" የተባሉት ለፈርኦንና ለሰራዊቱ እንጂ መች ለቀዳማዊ ምንሊክና ለዘሩ "ፈላሾች" መች ትሆናላችሁ አለ። በዚህ ላይ እኚህ "ፈላሾች" ፈልሰውበት የነበረው ቦታ የታላቁ ነብይ በሂብሩው ቋንቋ "ሙሼ ራቤኑ" ብለው የሚጠሩት የነብዩ ሙሴ ሚስት ሀገር፤ ንጉሳችን የሚሉት የንጉሥ ዳዊት ልጅ፣ የሰሎሞን ልጅ፣ የምንሊክ ሀገር ኢትዮጵያ ነው በክብር የተቀመጡበት። ይህንን ደግሞ እነርሱም ሆነ እነርሱ ያውቁታል። ይሄው "ጃ" ብለናል።
         ታዲያ እነዚህ "ጃ" ያልንላቸው ዘእምነገደ ይሁዳ የነጭ ይሁዳዊያን መጫወቻ ከሆኑ ዘመን ተቆጠረ ። ስንት ዘመን በኢትዮጵያ ጠብቀውት የነበረው እምነትና ስራታቸው እየተበረዘና ወደ ሌሎች እምነቶች እየተቀለበሰ ነው ። በዚህ ላይ አንዱ "ነጭ አማልእክት" ባሰኘው ጊዜ ይነሳና "እናንተ እውነተኛ ይሁዳዊያን አይደላችሁም፣ ተገረዙ፣ ልጅህና ልጄ አብረው ባንድ ክፍል አይማሩም  " ይላል ፤ ሌላው "ባለተራ አምላክ" ደግሞ  "ደምህን ደፋነው፤ እኔ በምዝናናበት ናይት ክለብ አትደረስ፣እኔም በምነዳው አውቶብስ አትሳፈር   "ይላል። ስንቱ ተዘርዝሮ ያልቃል።
         የዘንድሮው ደግሞ ሌላ ጉድ ነው። ምን ነበር የሚባለው "ጉድ ሳይሰማ  "መስከረም………. ቢጠባም ከፈላሾች መንደር የጉድ ዶፍ አላባራም።በጎንደር የሚገኙ ወደ እስራኤል ሀገራቸው ለመምጣት በመጠባበቅ ላይ ያሉ "ፈላሾች" የእርግዝና መከላከያ ካልወሰዳችሁ ወደ እስራኤል አትገቡም ሲባሉ ያለውድ በግዳቸው ወደ ሆዳቸው አንከባለሉት። ይህም ሳይበቃ እስራኤል ከመጡ በኋላ እንኳን ሳይቀር እንክብሎቹን እንዲወስዱ እየተገደዱ ነው።
       እነዚህ ወገኖቻችን በጎንደርና በአዲስ አበባ ከመንደራቸው ርቀው መጉላላታቸው መሰቃየታቸው ሳያንስ "ፍሬህን ወልደህ ለመሳም ኢሹር (ፍቃድ) ካልሰጠንህ ልትወልድ አትችልም" እያሉት ነው። የሚገርመው ነገር ከዛሬ ስልሳ ዓመት በፊት ጀምሮ  እነርሱ ከየነበሩበት ሀገር ወደ ተቀደሰችው ከነአን ሲገቡ ያለምንም ኢሹር ነበር፤ የእኛዎቹ "ፈላሾች"  ግን እስራኤል ለመድረስ የስንትና ስንት መስሪያ ቤት ቢሮና የባለስልጣን ኢሹር ያስፈልጋቸዋል። አረ ጎበዝ "ጃ" በል።
         ምድሪቱ እኮ የቃል ኪዳን ሀገርነቷ ለሁሉም የሀይሁድ ዘር ነው። እነርሱም የአብርሃም፣የይስሐቅ፣የያዕቆብ ልጆች ፤እነዚህም እንደዛው  ልጆች። ወይስ የእህተ ሙሴን እንጉርጉሮ ዛሬም ማዜም ፈልገው ነው። "ጃ" ብለናል "ሞአ ፈላሻ፣ ዘእምነገደ ይሁዳ"


No comments:

Post a Comment